“በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን በ230 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማ ሰሊጥ እየተሰበሰበ ነው” የዞኑ ግብርና መምሪያ

84

ሁመራ: መስከረም 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሰሊጥ በአማራ ክልል በስፋት ከሚመረቱ ምርቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ በክልሉ ሰሊጥ በስፋት ከሚመረትባቸው አካባቢዎች መካከል ደግሞ ወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ከቀዳሚዎቹ ይጠቀሳል፡፡ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን የሰሊጥ ሰብል ስብሰባ ተጀምሯል፡፡

የዞኑ ግብርና መምሪያ ኀላፊ አወቀ መብራቱ በዞኑ 230 ሺህ ሄክታር መሬት በሰሊጥ መሸፈኑን ገልጸዋል፡፡ የዝናቡ ሥርጭት የተመጣጠነ እንደነበር ያስታወሱት ኀላፊው የሰብል ቁመናው ጥሩ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ በዞኑ ሰሊጥ እየተሰበሰበ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 40 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማ ሰሊጥ ተሰብስቧል፡፡

በዞኑ ሲሊጥ በስፉት የሚሰበሰው ከመስረም 25 እስከ ጥቅምት 15 መኾኑን ኀላፊው አንስተዋል። በሰሊጥ ከተሸፈነው መሬት ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱንም አስታውቀዋል፡፡ የጉልበት ሠራተኞች በወቅቱ ወደ አካባቢው እንዲመጡ አስቀድመው ጥሪ ማቅረባቸውን ያስታወሱት ኀላፊው ሠራተኞቹ ወደ አካባቢው እየመጡ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ ሠራተኞች አስቀድመው አካባቢውን ስለሚያውቁት በቂ የሰው ኀይል እየገባ ነውም ብለዋል፡፡

ባለሃብቶች ለሠራተኞች እንክብካቤ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል፡፡ አብዘኛዎቹ ባለሃብቶች የሠራተኛ ደንበኞች ስላሏቸው አስቀድመው ጥሪ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል፡፡ አንዳንድ ባለሃብቶች የትራንስፖርት ወጪ እንደሚሸፍኑም ገልጸዋል፡፡

የንጹህ መጠጥ ውኃ አቅርቦት፣ የጤና አገልግሎት እና የምግብ አቅርቦት የተመቻቸ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ በዞኑ የተሟላ ሰላም እና አግልገሎት በመኖሩ ለሰብል አሰባሰቡ ምቹ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ ባለው የሰብል አሰባሰብ እንቅስቃሴ እና በሰብል አያያዝ ደስተኞች መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡

የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሕዝብ በአንድ በኩል ሰላሙን እየጠበቀ በሌላ በኩል በልማት ተጠቃሚነቱን እያረጋገጠ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ በዞኑ ከዓመት ዓመት የምርት እድገቱ እየጨመረ እንደሚገኝም አንስተዋል፡፡ በሰብል ልማት ብቻ ሳይኾን በእንስሳት ሃብት ልማት እና በሌሎች የልማት ዘርፎች ወጣቶች ተጠቃሚ እና ደስተኞች እንደኾኑም ተናግረዋል፡፡

በምርት ዘመኑ መታረስ ከሚገባው መሬት 98 በመቶው በሰብል መሸፈኑንም አስታውቀዋል፡፡ ወጣቶች እና ባለሃብቶች ከመቸውም በላይ ተደራጅተው ልማታቸውን እያለሙ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ የአካባቢው አርሶ አደር ዘመናዊ የእርሻ መሳሪያዎችን እና የሰብል መሰብሰቢያዎችን እንደሚጠቀምም ተናግረዋል፡፡

ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የበለጠ እንዲጠቀም እንቅስቀሴዎች መኖራቸውንም አመላክተዋል፡፡ ሰሊጥን ከባሕላዊ የአተራርስ እና አሰባሰብ ሂደት ማውጣት እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ በሂደት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን የመጠቀም ሥራ ይሠራልም ብለዋል፡፡

በዞኑ ከሰሊጥ ባለፈ ማሽላ፣ አኩሪ አተር እና ጥጥ በስፋት እንደሚመረቱም መምሪያ ኀላፊው ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየሕገ-መንግሥት ትርጉምና ውሳኔ አፈፃፀም ክትትል ቋሚ ኮሚቴ ከሕገ መንግሥት ትርጉም ጋር በተያያዘ በቀረቡ አቤቱታዎች ላይ ምርመራ አካሄደ።
Next articleሉሲዎቹ ከኢኳቶሪያል ጊኒ አቻቸው ጋር አቻ ተለያዩ።