
ባሕር ዳር: መስከረም 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በባለፈው ዓመት ሁለቱ ክለቦች የዋንጫ ተፎካካሪዎች ነበሩ ምንም እንኳን በመጨረዎቹ ሳምንታት ሲቲ በማሸነፍ አርሰናል ደግሞ በመሸነፍ አልያም ነጥብ በመጋራት የዋንጫው የድል ባለቤት የፔፖ ጋርዲዮላ ቡድን ቢሆንም።
በስምንት ሳምንት የዘንድሮው ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች መድፈኞቹ እስካሁን ሽንፈትን አላስተናገዱም። ውኃ ሰማያዊ ለባሾቹ ግን ባለፈው ሳምንት በወልቭስ ተሸንፈዋል። በደረጃ ሰንጠረዡ ላይም ሲቲዎች ስምንት ጨዋታ አድርገው በ20 ነጥብ አንደኛ ከኾኑት ከቶትንሃም ቀጥሎ ሁለተኛ ናቸው በ18 ነጥብ። መድፈኞቹም በአንድ ነጥብ ዝቅ ብለው ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
ስለጨዋታው አስተያየት የሰጡት የሲቲው አሠልጣኝ ጋርዲዮላ አርሰናሎች አሁን ወደ ተፎካካሪነት ተመልሰዋል፤ ወጣት ኾኘ ባርሴሎናን ማሠልጠን ስጀምር ከሰር አሌክስ ፈርጉሰን ማንቸስተር ዩናይትድ ጋር ያደርጉት የነበረውን ትንቅንቅ አስታውሳለሁ። ለብዙ ዓመታት በዚህ ተፎካካሪነታቸው ላይ አልነበሩም። አሁን ላይ ግን አቋማቸው ተመልሷል ብሏል።
መድፈኞቹ ከውኃ ሰማያዊ ለባሾቹ ጋር ያደረጓቸውን ያለፉት 12 የፕርምየር ሊግ ጨዋታዎች አላሸነፉም። ነገር ግን የኮሚኒቲ ሽልድ ዋንጫን ሲቲዎችን በፍጹም ቅጣት ምት ድል አድርገው ዋንጫውን ወስደዋል።
የመድፈኞቹ አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ ሲቲን በኢምሬትስ ስታዲየም በደጋፊያቸው ፊት እንደሚያሸንፊ በቡድኑ ጥንካሬ ያምናል።
አርቴታ እንደሚለው የሲቲዎች የተጫዋቾች ብቃት ያሳስበኛል ፤ ሙሉ ጊዜያችንን ለጨዋታው መስጠት አለብን ፤ ከእኛ የሚጠበቀው ለጨዋታው ትኩረት ሰጥቶ በመጫወት ማሸነፍ ነው ብሏል።
በአርሴናል በኩል ጋብርኤል ማርቲኔሊ በጉዳት አይሰለፍም። ቡካዮ ሳካ በቻምፒዮንስ ሊጉ ከሌንስ ጋር በነበረው ጨዋታ ጉዳት አጋጥሞታል በዚህም ምክንያት ላይሰለፍ ይችላል። የእግርኳስ ተንታኙ ክሪስ ሱተን ሁለቱ ተጫዋቾች በሙሉ ብቃት በዚህ ጨዋታ ቢሰለፉ ለመድፈኞቹ የበለጠ ዕድል ይኖረው ነበር ብሏል።
ሲቲዎች የአማካይ ተጫዋቻቸው ሮዲሪን በጉዳት ምክንያት አያሰልፉም። በተመሳሳይ ጆን ስቶንስ እና ኬቨን ዲብሩይን አይሰለፉም።
በሌላ በኩል የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪዎች በ8 ግብ እየመራ ያለው ኤርሊንግ ሃላንድም ባለፉት አራት ጨዋታዎች አንድ ጎል ብቻ ነው ያስቆጠረው። ሃላንድ አሁንም ግን አደገኛ ተጫዋች ነው።
የመድፈኞቹ አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ እስካሁን ከሲቲ ጋር ያደረጋቸውን 7 ጨዋታዎች ተሸንፏል። ሁለቱ ቡድኖች ካደረጓቸው ያለፉት 16 የፕርምየር ሊግ ጨዋታዎች አርሰናል ማሸነፍ አልቻሉም። በተከታታይ በ12ቱ ጨዋታዎችም ተሸንፈዋል።
ኾኖም ግን ዘንድሮ በሊጉ በአምስት ጨዋታ አሸንፈው በሁለቱ አቻ ወጥተው በጥሩ ጥንካሬ ነው ሲቲን የሚያገኙት። በቀላሉ እጅ ለሲቲ አይሰጡም።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ዛሬ 12:00 በኢምሬትስ ስታዲየም ይደረጋል።
በአወል ከበደ
ማን ያሸንፋል? የእርስዎን ግምት ያጋሩን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!