
ባሕር ዳር: መስከረም 27/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በአህጉራዊው የእግር ኳስ መድረክ የነበራት ውክልና “መሥራች” የሚል የማዕረግ እና የክብር ሥም የሚሰጠው ነበር፡፡ ምንም እንኳን አሁናዊው የሀገሪቷ የእግር ኳስ ደረጃ ከተሳትፎ የዘለለ ባይሆንም እግር ኳስን እንደነፍሳቸው የሚወዱት ብርቱ እና ታታሪ ደጋፊዎቿ አሁንም ድረስ ድምቀት ናቸው፡፡
የሀገሪቱን ብሔራዊ ቡድን ለመደገፍ በአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ሰንደቀ ደምቀው፤ ብሕብረ ዝማሬ አሸብርቅው ብቅ ሲሉ የውድድር መድረኮቹ ድምቀት ሆነው ይታያሉ፡፡ ኢትዮጵያን በብሔራዊ ቡድኗ ብቃት እና ውጤት የሚያስታውስ ባይኖር እንኳን የደጋፊዎቿን ፍጹም የእግር ኳሱ ዓለም ታማኝነት የሚዘነጋ ግን አይኖርም፡፡ ኢትዮጵያ ባለችበት የእግር ኳሱ ዓለም ፉክክር ያለማጋነን ደጋፊዎቿ ክስተት ሆነው ብቅ ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ ከእግር ኳሱ ዓለም ወደ ኋላ እየተንሸራተተች መጥታ አሁን ካለችበት ደረጃ ላይ መድረሷ ለደጋፊዎቿ ብሽቀት እና ለዓለም የእግር ኳስ ቤተሰቡ ደግሞ ናፍቆት ነው፡፡ ስለምን ከሌሎቹ የአፍሪካ ሀገራት ቀድማ መጥታ በጊዜ ጠፋች ሲሉ የሚጠይቁት የእግር ኳሱ ቤተሰቦችም በርካቶች ናቸው፡፡ ለሀገሪቷ የእግር ኳሱ ዘርፍ መዳከም በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም አንዱ ተጠቃሽ ምክንያት ግን ጠንካራ ክለብ አለመኖሩ ነው ይባላል፡፡
የሀገር ውስጥ የክለቦች ውድድር የብሔራዊ ቡድኑን ያክል የደረጀ መሠረትም ሆነ እድሜ ያለው ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡ ጠንካራ የሆነ የውስጥ ሊግ አለመኖሩ ከእነድክመቱ እንዳለ ኾኖም የውድድሩ ተደጋጋሚ አሸናፊዎች እና የደረጃ ሰንጠረዡ መሪዎች በእጣት የሚቆጠሩ ክለቦች ናቸው፡፡ ይኽም የችግሩን ሥር የሰደደ መሆን አመላካች ሆኖ ይቀርባል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የውስጥ ውድድሩን አቀራረብ በተወሰነም ደረጃ ቢኾን አሻሽሎ በቀረበው የኢትዮጵያ ፕሪሜር ሊግ ውድድር ውስጥ ብዙም ሥም እና ዝና የሌላቸውን ክለቦች ወደ አሸናፊነት ብቅ ሲሉ ይስተዋላል፡፡ አዳዲስ የፕሪሜር ሊጉ አሸናፊዎች እና በደረጃ ሰንጠረዡ ውስጥ ከመሪዎቹ ተርታ የሚሰለፉ ክለቦች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ ከመቀሌ ሰባ እንድርታ እስከ ጅማ አባጅፋር፤ ከፋሲል ከነማ እስከ ባሕር ዳር ከነማ የሊጉ አዳዲስ ክስተቶች እና ድምቀቶች ኾነው ብቅ ብቅ ሲሉ ታይቷል፡፡ ጥያቄው ያገኙትን እና ያስመዘገቡትን እድል ምን ያክል እያስቀጠሉ ነው የሚለው ነው፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ ፕሪሜር ሊግ ክስተት ከሆኑ ክለቦች መካከል አንዱ ባሕር ዳር ከነማ ነው ያሉን የክለቡ ዋና አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ናቸው፡፡ ባለፉት ቅርብ ዓመታት የክለቡ ታሪክ የሚነግረን ከሊጉ ላለመውረድ የሚደረግ ጥረት ነበር የሚሉት አሰልጣኙ በ2015 የውድድር ዘመን ግን በአስገራሚ ብቃት እስከ መጨረሻው ጨዋታ ድረስ ለዋንጫ የሚጫዎት ክለቡ ለመሆን በቅቷል፡፡
አሰልጣኙ ባሕር ዳር ከነማ በውድድር ዓመቱ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ከማጠናቀቁ በተጨማሪ በክለቡ ታሪክ አዳዲስ የኾኑ በርካታ ስኬቶችንም አስመዝግቧል ይላሉ፡፡ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ለተለያዩ የብሔራዊ ቡድኑ ውድድሮች እስከ 9 ተጫዋቾችን ማስመረጥ ችሏል፡፡ በውድድር ዓመቱ ስኬታማ ጉዞ ለኮከብ ተጫዋቾች ምርጫ ሦስት እጩዎችን ሲያስመርጥም የመጀመሪያው እንግዳ ክስተት ነበር፡፡
በውድድር ዓመቱ ያስመዘገበውን ስኬታማ ውጤት ተከትሎ ከሀገራዊ ውድድሮች አልፎ በአህጉራዊ ውድድር የመሳተፍ እድል ሲያገኝ በታሪኩ የመጀመሪያው ኾኖ ተመዝግቧል፡፡ በክለቡ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በሊጉ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ማጠናቀቁን ተከትሎ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ የመሳተፍ እድልን አሳካ፡፡
በመጀመሪያ ማጣሪያ ውድድሩም በአፍሪካ ክለቦች ውድድር የላቀ ሥም እና ዝና ያለውን የታንዛኒያውን ክለብ አዛምን በደርሶ መልስ ውጤት አሸንፎ ወደ ቀጣዩ የማጣሪያ ውድድር ማለፍ ቻለ፡፡ የአዛምን የገዘፈ ታሪክ እና ዝና የሚያውቁ የእግር ኳሱ ቤተሰቦች ይኽ ይሆናል ብለው አልገመቱም ነበር፡፡
በቀጣዩ የማጣሪያ ውድድርም ባሕር ዳር ከነማን የገጠመው ክለብ በአፍሪካ የእግር ኳስ ክለብ የካበተ ልምድ እና ከ100 ዓመታት በላይ የምሥረታ ታሪክ ያለው ክለብ ነበር፡፡ ከቱኒዚያው ክለብ አፍሪካ ጋር የተገናኘው የአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ክለብ በበርካታ መሰናክሎች መካከል አልፎ እና በሀገሩ ያለደጋፊዎቹ ጉምቱውን ክለብ አስተናግዶ 2 ለ 0 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡
ከክለብ አፍሪካ ጋር በቱኒዚያ የተደረገው የመልስ ጨዋታ እጅግ በርካታ መሰናክሎች የነበሩበት ነበር የሚሉት አሰልጣኙ በጸጥታ ችግር ምክንያት የልምምድ መርሐ ግብሩን በአዲስ አበባ እንዲያደርግ ተገድዷል ይላሉ፡፡ በሜዳ እጦት የልምምድ መርሐ ግብሮቹን እስከ መሰረዝ የደረሰው ባሕር ዳር ወደ ቱኒዚያ ለማቅናት መሰናክሎች ገጥመውት እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ከነፈተናዎቹ ወደ ቱኒዚያ አቅንቶ በተጋጣሚው ክለብ ደጋፊዎች እና ሜዳ እስከ መጨረሻው 90 ደቂቃዎች ተፋልሞ በጠባብ የደርሶ መልስ 3 ለ 2 ውጤት ወደ ቀጣዩ ዙር ሳያልፍ ቀርቷል፡፡
አሰልጣኝ ደግአረገ ባሕር ዳር ከነማ ከውድድር ዓመቱ የላቀ ስኬት ጀርባ የበርካታ ባለድርሻዎች በጎ ተፅዕኖ የጎላ ነበር ይላሉ፡፡ ጽኑዎቹ የክለቡ የልብ ደጋፊዎች፣ የክለቡ የቦርድ የበላይ የሥራ ኅላፊዎች፣ እግር ኳስ ወዳዱ ሕዝብ፣ አጋር ድርጅቶች፣ የብዙኅን መገናኛ ተቋማት፣ የአሰልጣኞች ቡድን እና የክለቡ አባላት የተገኘው ውጤት ባለቤቶች ናቸው ይላሉ፡፡ ከምንም በላይ ግን በእያንዳንዷ ጨዋታ ስፖርታዊ ሥነ-ምግባር እና የአልሸነፍም ባይነት ስሜት የተላበሱት ተጫዋቾቹ የክለቡ ታሪካዊ ድል ባለቤቶች ነበሩ ብለዋል፡፡
ከአህጉራዊ ውድድሮች መልስ በ2016 የውድድር ዓመት ጅማሮ ዋዜማ ላይ ያለው ባሕር ዳር ከነማ ያለፈውን ዓመት ስኬት ለማስቀጠል አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ዝግጅት አድርጓል ተብሏል፡፡ በአህጉራዊ ውድድሮቹ በርካታ መሰናክሎች ነበሩብን ያሉት አሰልጣኙ ችግሮቹ የሚፈቱት ግን በክለቡ ደጋፊዎች፣ የቦርድ አባላት እና በአጋር ድርጅቶቹ ነው ይላሉ፡፡
እግር ኳስ በሰጡት ትኩረት ልክ መልሶ የሚሰጥ እና ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚፈልግ ዘርፍ ነው፡፡ አሰልጣኑ ባሕር ዳር ከነማ ከከተማ አስተዳደሩ በጀት፣ ከመንግሥት ድጎማ እና ከውስን የአጋር አካላት ተሳትፎ በተጨማሪ ጠንካራ የገቢ ምንጭ እንዲኖረው መሥራት የግድ ይላል ብለዋል፡፡ የክለቡ ደጋፊዎች የክለቡ የጀርባ አጥንት በመሆናቸው ለክለቡ ስኬት አብረው እንዲዘልቁም አሳስበዋል፡፡
ተጫዋቾችን ጨምሮ የቡድኑ አባላት ባለፈው የውድድር ዓመት የተገኘውን ስኬት በ2016 የውድድር ዓመትም በላቀ ደረጃ ለመድገም ዝግጁ ናቸው ብለዋል አሰልጣኙ፡፡ ክለቡ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ተቀራርቦ በጋራ ለመሥራት ይፈልጋል፤ ኑ እና በጋራ እንስራ “ሞገዱን ደግፉም” ብለዋል፡፡
በታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!