“በ190 ቀበሌዎች የወባ መከላከያ ኬሚካል ርጭት ሊካሄድ ነው” የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

36

ባሕር ዳር: መስከረም 27/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት አሳሳቢ እየኾነ የመጣውን የወባ ሥርጭት መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ከጤና ባለሙያዎች እና ከሥራ ኀላፊዎች ጋር በባሕር ዳር ውይይት አካሂዷል፡፡

በክልሉ 82 በመቶ የሚኾነው የኅብረተሰብ ክፍል ለወባ ስርጭት ተጋላጭ መኾኑም በውይይቱ ተነስቷል። በክልሉ ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ የወባ ስርጭት እየጨመረ እንደሚገኝም ተጠቁሟል፡፡

በ2010 ዓ.ም 280 ሺህ ገደማ የነበረው የወባ ሕሙማን ቁጥር በ2015 ዓ.ም ከ1 ነጥብ 1 ሚሊዮን በላይ መድረሱ በማሳያነት ተነስቷል፡፡

በተለይም የክልሉ ምዕራባዊ አካባቢዎች በከፍተኛ ሁኔታ የወባ ስርጭት እየጨመረ መጥቷል ተብሏል፡፡

በክልሉ የሚገኙ 30 ወረዳዎች ደግሞ 72 በመቶ የክልሉን የወባ ስርጭት ይሸፍናሉ ነው የተባለው፡፡ ከእነዚህ ወረዳዎች መካከል ምሥራቅ ደምቢያ አንዱ ነው፡፡

ወረዳው በ1949 ዓ.ም በአካባቢው ከፍተኛ የወባ ወረርሽኝ ተከስቶ የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል፡፡ የወረዳ ጤና ጥበቃ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ወርቅነህ ታከለ ወረዳው የጣና ሐይቅ አዋሳኝ፣ የበርካታ ወንዞች እና የመስኖ ፕሮጀክቶች መገኛ በመኾኑ ለወባ ሥርጭቱ ምቹ ሁኔታ ፈጥሯል ብለዋል፡፡

ከ1 ሺህ ሰዎች መካከል 63ቱ በወባ በሽታ እንደሚጠቁ ያነሱት ኀላፊው በዞኑ በወባ ሥርጭት በቀዳሚነት እንዲቀመጥ አድርጎታል ነው ያሉት፡፡

ኀላፊው እንዳሉት በሽታውን ለመከላከል የቤት ለቤት የአጎበር አጠቃቀም ግንዛቤ ፈጠራ ሥራ ተሰርቷል። ከፍተኛ የወባ ሥርጭት ባለባቸው የጣና ተፋሰስ ቀበሌዎች የቁጥጥር ሥራ እየተሠራ ይገኛል። የወባ የሕክምና አገልግሎት እየተሰጠ ነው፡፡ ይሁን እንጅ አሁንም ድረስ ኬሚካል እርጭት አለመካሄዱ ለሥርጭቱ መባባስ እንደ አንድ ምክንያት ተነስቷል፡፡

የአማራ ክልል ኅብረተሰብ ጤና ኢንስትቲዩት የወባ ፕሮግራም አስተባባሪ ዳምጤ ላንክር እንዳሉት በክልሉ የወባ ስርጭትን ሪፖርት ማድርግ ከሚጠበቅባቸው 5 ሺህ 102 የጤና ተቋማት ውስጥ 70 በመቶው ለኢንስትቲዩቱ ሪፖርት አድርገዋል ብለዋል፡፡

ሪፖርት ካደረጉት ውስጥ 90 በመቶ የሚኾነውን የወባ ስርጭት የሚሸፍነው የክልሉ ምእራባዊ ክፍል እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ በየአካባቢው የቁጥጥር ሥራ አለመሠራት፣ ወቅቱን የጠበቀ የኬሚካል ርጭት አለማካሔድ፣ የወባ መራቢያ ቦታዎችን የቁጥጥር ሥራ አለመሠራት እና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ለሥርጭቱ መጨመር በምክንያትነት ተቀምጠዋል፡፡

ከዚህ በፊት በስድስት ወረዳዎች ላይ ርጭት መካሄዱን የገለጹት አሥተባባሪው በቀጣይ በ190 ቀበሌዎች የኬሚካል ርጭት ለማካሔድ ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቅቁን ገልጸዋል፡፡

በ2015 ዓ.ም እስከ አምስት ዓመት የሚያገለግል ለ6 ሚሊዮን የኅብረተሰብ ክፍሎች አጎበር ሥርጭት ተካሂዷል፡፡ መተኪያ ለሚያስፈልጋቸው አካባቢዎችም ለማቅረብ እየተሠራ መኾኑን ነው ያነሱት፡፡

ከመስከረም እስከ ታሕሳስ ያሉት ወራት በከፍተኛ ሁኔታ ወባ የሚከሰትባቸው ወቅቶች በመኾናቸው መድኃኒት አቅራቢ ድርጅቶች መድኃኒት እንዲያቀርቡም ጠይቀዋል፡፡

ማኅበረሰቡም የአካባቢ ቁጥጥር ሥራ ላይ ትኩረት እንዲያርግ እና የተሰራጨውን አጎበር በአግባቡ እንዲጠቀም አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየኢሬቻ በዓል በሰላም መጠናቀቁን የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረኃይል ገለጸ።
Next article“የ2015ዓ.ም የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት ነገ ይፋ ይኾናል” ትምህርት ሚኒስቴር