“ከአኩሪ አተር የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን ማዘጋጀት ይቻላል” የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል

21

ገንዳ ውኃ: መስከረም 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከአኩሪ አተር ምርት የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን በማዘጋጀት ለማኅበረሰቡ እያስተዋወቀ መኾኑን የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል አስታውቋል፡፡ የአኩሪ አተር ሰብል በሀገሪቱ ቆላማ አካባቢዎች በስፋት እየለማ ይገኛል። ይህ የሰብል ዓይነት ለውጭ ገበያ፣ ለኢንዱስትሪ እና ለፋብሪካዎች በግብዓትነት ከመቅረብ የዘለለ እንደ ሌሎች ምርቶች ለምግብነት አልተለመደም ነበር። አኩሪ አተር በስፋት ከሚለማባቸው አካባቢዎችም የምዕራብ ጎንደር ዞን ተጠቃሽ ነው። የዞኑ አርሶአደሮች እና አልሚ ባለሃብቶች ሰብሉን በስፋት ያምርቱት እንጅ ለገቢያ ከማዋል ያለፈ ቤታቸው ውስጥ ለምግብ ፍጆታነት ሲጠቀሙት አይስተዋልም።

የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ምርቱ ለቤት ውስጥ የምግብ ፍጆታ እንዲውል በምዕራብ ጎንደር ዞን ለሚገኙ ነዋሪዎች የተግባር ሥልጠና እየሰጠ እና ምግቡን እያስተዋወቀ ይገኛል። ከአኩሪ አተር ምርት ወተት፣ ዳቦ፣ እንጀራ እና ወጥን ጨምሮ ከ15 በላይ የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን በማዘጋጀት ለማኅበረሰቡ እያስተዋወቀ መኾኑን የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ምንተስኖት ወርቁ አስታውቀዋል።

የማኅበረሰቡን የአመጋገብ ሥርዓት ከማሻሻል ባሻገር በአኩሪ አተር ምርት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንደሚቻል ጥሩ ማሳያ ነው ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡ የሥልጠናው ተሳታፊዎች በበኩላቸው የአኩሪ አተር ሰብልን ባለፈው ዓመት በስፋት ያምርቱት እንጅ የመሸጫ ዋጋ መውረድ ከፍተኛ የኾነ ምጣኔ ሃብታዊ እና ስነ ልቦናዊ ጫና እንዳሳደረባቸው አውስተዋል፡፡

ከሥልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ ካላይታ በሪሁን ከምርምር ማዕከሉ ባገኙት ሥልጠና መሠረት ምርቱን ቤታቸው ውስጥ ለተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን በማዘጋጀት እንደሚጠቀሙበት ተናግረዋል፡፡ ምርቱ ለምግብነት በመዋሉም የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥ እንደሚያስችላቸውም ነው የገለጹት። በስልጠናው ያገኙትን ዕውቀት እና ልምድ ቤታቸው ውስጥ ተግባራዊ ከማድረግ ባሻገር ለጎረቤቶቻቸው የምግብ አዘገጃጀት ሂደቱን እንደሚያሰለጥኑም አረጋግጠዋል።

ሌላኘው ተሳታፊ አርሶ አደር ብርቱካን እንየው በተፈጠረው የመሸጫ ዋጋ መውረድ በዚህ ዓመት ሰብሉን በስፋት አለማልማታቸውን ነው የተናገሩት። ይሁን እንጅ አሁን ላይ ለምግብነት በመዋሉ በቀጣይ ሰብሉን በስፋት ለማልማት መነሳሳትን እንደፈጠረላቸው ገልጸዋል። ተቋሙ በሥነ ምግብ አዘገጃጀቱ እያበረከተው ስላለው ተግባር አመሥግነዋል፡፡ ሥልጠናው በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ እንዲኾንም ጠይቀዋል።

በጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል የአኩሪ አተር ሰብል ተመራማሪው አቶ ጎበዜ ጫቅሌ እንደሚሉት የአኩሪ አተር ሰብል ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ሳይንሳዊ ጥናት ያረጋግጣል። ነገር ግን ምርቱን ለሀገር ውስጥ የምግብ ፍጆታ በማዋል እና ለማኅበረሰቡ በማስተዋወቅ ረገድ የግንዛቤ ክፍተቶች እንዳሉ ይናገራሉ። የአኩሪ አተር ሰብል ከምጣኔ ሃብታዊ ፋይዳው ባሻገር የአፈር ለምነትን በማሳደግ ምርትና ምርታማነት እንደሚጨምርም ተመራማሪው ገልጸዋል።

አኩሪ አተር በውስጡ በርካታ ንጥረ ነገሮችን በመያዙ ለጤና ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው:: የምግብ አዘገጃጀት ሥልጠናው እና ምግቡን የማስተዋወቅ ተግባሩ በዞኑ ባሉ ሁሉም የገጠር ቀበሌዎች ተደራሽ እንደሚደረግም የማዕከሉ ዳይሬክተር አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ፡- ቴዎድሮስ ደሴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየግሪሳ ወፍን ለመከላከል በአውሮፕላን የታገዘ ኬሚካል ርጭት መጀመሩን የቀወት ወረዳ አሥተዳደር አስታወቀ፡፡
Next articleየኢትዮጵያን እና አሜሪካን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያስችል ውይይት ተካሂዷል።