‹‹ኢትዮጵያ በመከባበር፣ በመተሳሰብና በአንድነት የምንኖርባት እንጂ የአጋችና ታጋች መኖሪያ ሀገር አይደለችም፡፡›› የሰቆጣ ከተማ ሠላማዊ ሰልፈኞች

139

የታገቱ የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሰላም እንዲፈቱ እና መንግሥት በአጋቾች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንዲወስድ የሰቆጣ ከተማ ሠላማዊ ሰልፈኞች ጠየቁ፡፡

ነዋሪዎቹ ዛሬ ረፋድ ላይ የእገታ ድርጊቱን በማውገዝ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡ የሰልፉ አስተባበሪ አቶ ሀብታሙ መንግሥቴ ድርጊቱ ለኢትዮጵያዊነት እና ለ21ኛው ክፍለ ዘመን የማይመጥን ፀረ ሰላም ተግባር በመሆኑ ኅብረተሰቡ ማውገዙን ተናግረዋል፡፡ መንግሥት እገታውን በፈጸሙ አካላት ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ እንዳለበት ሠላማዊ ሰልፈኞቹ መጠየቃቸውን ለአብመድ የገለጹት አቶ ሀብታሙ መሰል ድርጊቶች እንዳይፈጠሩ አስቀድሞ መከላከል ላይ ሊሠራ እንደሚገባ ማሳሰባቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

አቅም የሌላቸው ሴቶችንና ተማሪዎችን ለተለየ ጥቅም ማገት ከኢትዮጵያዊነት እሴት ያፈነገጠና ኢ-ሰብዓዊ እንደሆነም ነው የሠላማዊ ሰልፉ አሥተባባሪ የተናገሩት፡፡

እንደዚህ አይነት ድርጊት የሚሠሩ ቡድኖች አቅም እንዳይጎለብት እና በሕዝብ ላይ የከፋ ጉዳት እንዳይደርስ መንግሥት እንዲሠራ በሠልፉ አጽንዖት ተሰጥቶ እንደተጠየቀም ነው አቶ ሀብታሙ የገለጹት፡፡

ዛሬ በሰቆጣ ከተማ በተካሄደው ሠላማዊ ሰልፍ ‹‹ኢትዮጵያ በመከባበር፣ በመተሳሰብና በአንድነት የምንኖርባት እንጂ የአጋችና ታጋች መኖሪያ ሀገር አይደለችም፤ ፍትሕ ለታገቱ ተማሪዎች፤ መንግሥት የዚህን ታሪክ ምዕራፍ ይዝጋልን፤ ሰላማችንን ለማደፍረስ የሚሠሩ ኃይሎችን ማባበል ይብቃ!›› የሚሉ መልዕክቶች ተሥተጋብተዋል፡፡ ሠላማዊ ሠልፉም በሠላም እንደተጠናቀቀ ታውቋል፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

Previous articleየደብረ ታቦር ከተማ አሥተዳድር ነዋሪዎች በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ የተፈጸመውን የእገታ ድርጊት እያወገዙ ነው፡፡
Next articleየኮምቦልቻ ከተማ አሥተዳድር ነዋሪዎች በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ የተፈጸመውን የእገታ ድርጊት አወገዙ፡፡