የግሪሳ ወፍን ለመከላከል በአውሮፕላን የታገዘ ኬሚካል ርጭት መጀመሩን የቀወት ወረዳ አሥተዳደር አስታወቀ፡፡

32

ደብረ ብርሃን: መስከረም 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ሽዋ ዞን ቀወት ወረዳ የተከሰተው የግሪሳ ወፍ በሰብል ላይ ጉዳት ሳያደርስ ለመከላከል በአውሮፕላን የታገዘ የኬሚካል እርጭት ተጀምሯል፡፡ የቀወት ወረዳና አካባቢው በጤፍና ማሽላ ሰብል ትርፍ አምራች ከሚባሉ አካባቢዎች መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡ በየዓመቱ የሚከሰተው የግሪሳ ወፍ አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ ካልተደረገ የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ ነው ተብሏል፡፡ በዚህ ዓመትም በወረዳው በአምስት ቀበሌዎች የግሪሳ ወፍ መከሰቱን ከወረዳው ግብርና ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

የተከሰተው የግሪሳ ወፍ ጉዳት እንዳያደርስ እስከ ግብርና ሚኒስቴር ድረስ የቅድመ ዝግጅት ሥራ ሲደረግ እንደቆየ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሽመልስ ችሮታው ተናግረዋል፡፡ ከትናንት ጀምሮ የኬሚካል ርጭት መጀመሩን የተናገሩት ዋና አሥተዳዳሪው ማኅበረሰቡም ከወቅታዊ የጸጥታ ችግሮች ጎን ለጎን ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል ብለዋል።

በዚህ ዓመት የግሪሳ ወፍ ቀድሞ የተከሰተ መሆኑን የተናገሩት ዋና አሥተዳዳሪው እርጭቱ ሲካሄድ ከእንሰሳት ሃብት አንጻር ጉዳት እንዳያስከትል አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ እየተደረገ ስለመሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ዘጋቢ ፡- በላይ ተስፋዬ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድምና እህት ሕዝቦች ጋር በፍቅርና በአብሮነት የሚያከብረው በዓል ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next article“ከአኩሪ አተር የተለያዩ የምግብ ዓይነቶችን ማዘጋጀት ይቻላል” የጎንደር ግብርና ምርምር ማዕከል