
ባሕርዳር፡ መስከረም 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የኢሬቻ በዓልን ምክንያት በማድረግ ለመላው የኦሮሞ ሕዝብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡አቶ አረጋ በመልዕክታቸው “ለመላው የኦሮሞ ሕዝብ እንኳን ለ2016 ዓ.ም የኢሬቻ በዓል በሠላም አደረሳችሁ” ብለዋል፡፡
ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ክረምቱን በሰላም ማለፉን፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን በሰላም መሸጋገሩን፣ አዲስ ዓመት መበሰሩን መሠረት በማድረግ ለፈጣሪው ምስጋና የሚያቀርብበትና አክብሮቱን የሚገልፅበት በዓል ነው ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ። የኢሬቻ በዓል የኦሮሞ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድምና እህት ሕዝቦች ጋር በሠላም፣ በፍቅር፣ በመቻቻልና በአብሮነት የሚያከብረው የአደባባይ በዓል ነውም ብለዋል። በመሆኑም ለመላ የኦሮሞ ሕዝብ በዓሉ የፍቅር፣ የሠላም፣ የጤና፣ የመቻቻል እና የአብሮነት በዓል እንዲሆን እመኛለሁ ሲሉ መልካም ምኞታቸውን መግለፃቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!