“ሰላም እና መረጋጋት ላይ ካልተሠራ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴው ይረጋጋል ብሎ ማሳብ አስቸጋሪ ነው” ፋንታሁን ባይሌ (ዶ.ር)

30

ባሕር ዳር: መስከረም 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሰላም ሲናጋ የሀገር እና ሕዝብ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ምጣኔ ሃብታዊ ሥርዓት ይናጋል፡፡ ዜጎች የዓመት ልብሳቸውን እና የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት ይቸገራሉ፡፡ የኑሮ ውድነት ከገቢ አቅም እየቀደመ ኑሮን እያወሳሰበው ይሄዳል፡፡

አልጣጣም ያለውን ፍላጎት እና አቅርቦት ሚዛን ለማስጠበቅ ሰላም ቀዳሚው ጉዳይ ነው፡፡ ሰላም ከሌለ ፍላጎት እየጨመረ አቅርቦት ደግሞ እየቀነሰ ይሄዳል፡፡ በዚህም ምክንያት የኑሮ ውድነት በእጅጉ ይባባሳል፡፡ በጎንደር ዪኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት ሳይንስ መምህር እና ተመራማሪ ፋንታሁን ባይሌ (ዶ.ር) ምጣኔ ሃብታዊ ሥርዓቱ በሚፈለገው መልኩ እንዲሠራ የሰላም እና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ሥርዓትን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል፡፡ የኑሮ ውድነትን እና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት ሰላም ወሳኝ ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡የሚፈጠሩ ሀገራዊ ችግሮች ለመፍታት ከኃይል ባሻገር ያሉ አማራጮችን መመልከት እና እነርሱን መጠቀም እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ የሕዝብ ጥያቄዎችን በአስቸኳይ እየፈቱ ወደ መደበኛ የሥራ እንቅስቃሴ መግባት እና ምጣኔ ሃብትን ማስተካከል ይገባል ነው የሚሉት፡፡

የመንገድ እና መሠረተ ልማት አገልግሎት መዘጋጋት ምጣኔ ሃብቱን እንደሚጎዳውም ተናግረዋል፡፡ ምጣኔ ሃብታዊ ሥርዓቱን መስመር ለማስያዝ እና የኑሮ ውድነቱን ለመግታት ደግሞ ሰላም ላይ ሁሉም መሥራት አለበት ነው ያሉት፡፡ ለሀገራዊ ችግሮች አንድ ዓይነት የመፍትሄ አቅጣጫ ብቻ መከተል ችግሮችን ይበልጥ ያወሳስብ ካልኾነ በቀር መፍትሄውን ቅርብ እንደማያደርገውም ጠቁመዋል፡፡ የሕዝብ ጥያቄዎችን ለመፍታት አስቀድሞ ሰላምን ማረጋገጥ ግድ እንደሚልም ተናግረዋል፡፡ በየጊዜው የሚፈጠሩ ችግሮችን በውይይት እና በበሰለ መንገድ መፍታት ካልተቻለ መንግሥት እና የሀገር ሃብት ለፖለቲካዊ እና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ብቻ ስለሚውሉ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴው በእጅጉ ይጎዳል ነው ያሉት፡፡

ሰላም ሲጠፋ ሕገ ወጥ ንግድን፣ ሥርዓት አልባ የገበያ ሥርዓቱን እና ሌሎች ችግሮችን መቆጣጠር እንደማይቻልም ተናግረዋል፡፡ ሰላም ሲኖር እና የተረጋጋ ሀገራዊ አውድ ሲፈጠር ምጣኔ ሃብታዊ ችግሮችም ይስተካከላሉ ነው ያሉት፡፡ ክልሉ ሊረጋጋ በሚችልባቸው ጉዳዮች ላይ ጊዜ እና ትኩረት ሰጥቶ መሠራት እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡ የተረጋጋ አካባቢ መፍጠር ሲቻል አንዳንድ ምጣኔ ሃብታዊ ውስንነቶች በራሳቸው ወደ መደበኛው ሥርዓት እንደሚመለሱም አንስተዋል፡፡

የመሬት ወረራ፣ የዋጋ ንረት እና ሌሎች ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች የሰላም እጦት ምልክቶች ናቸው ያሉት የምጣኔ ሃብታዊ ተመራማሪው ሰላምና መረጋጋት ላይ ካልተሠራ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴው ይረጋጋል ብሎ ማሳብ አስቸጋሪ ነው ብለዋል፡፡ የኑሮ ውድነቱን ለመቋቋም ዜጎች በረጅም ጊዜ የሚመጣውን ለውጥ እየጠበቁ መፍትሄዎችን መመልከት አለባቸውም ብለዋል፡፡ ተጨማሪ የገቢ ምንጮችን መፍጠር እና ከኑሮ ውድነቱ ቀድሞ ሊሄድ የሚችል ሥራ መሥራት እና ገቢን ማሳደግ ይገባል ነው ያሉት፡፡

ሌላኛው የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም ብለው ያነሱት የመፍትሄ ምክረ ሃሳብ ወጪ እና አላስፈላጊ ብክንትን መቀነስ ነው፡፡ አላግባብ የሆኑ ወጪዎችን መቀነስ እና ገንዘብ መቆጠብ የኑሮ ውድነትን ለመቋቋም አማራጭ ይሆናል ነው ያሉት፡፡ የአኗኗር ዘይቤን መቀየርም ሌላኛው የኑሮ ውድነትን መቋቋሚያ መፍትሔ ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡ ለአብነት ጤፍን ያስወደደው የፍላጎትና የፍጆታ መጨመር ነው ያሉት ተመራማሪው የአመጋገብ ሥርዓትን ማስተካከል መልካም መሆኑን አንስተዋል፡፡

በአጭር ጊዜ የኑሮ ውድነቱን እና የዋጋ ንረቱን መቋቋም ስለማይቻል የራስን አቅም ማሳደግ ላይ በትኩረት መሥራት ይገባል ነው ያሉት፡፡ የኑሮ ውድነቱን ለመግታት መንግሥት ከሚሰጣቸው መፍትሔዎች ባሻገር የራስን መፍትሔ መውሰድ ግድ ይላል ብለዋል፡፡መንግሥት በወቅታዊ ጉዳዮች ሲጠመድ እና ቅድሚያ ለሚሰጣቸው ጉዳዮች ቅድሚያ ሲሰጥ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን በራስ አቅም የመፍታት አቅምን መለማመድ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleተማሪዎችን ወደ መደበኛው የትምህርት ገበታ ለመመለስ ማኅበረሰቡ ኅላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ፡፡
Next article“ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወንድምና እህት ሕዝቦች ጋር በፍቅርና በአብሮነት የሚያከብረው በዓል ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ