ተማሪዎችን ወደ መደበኛው የትምህርት ገበታ ለመመለስ ማኅበረሰቡ ኅላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ፡፡

20

ወልድያ: መስከረም 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሰሜን ወሎ ዞን በትምህርት ዘመኑ መማር ካለባቸው ተማሪዎች ውስጥ 68 በመቶ አንደኛ ደረጃ እና 50 በመቶ ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በመማር ላይ መኾናቸው ተገልጿል። የትምህርት ሚኒስቴር መስከረም 14/2016 ዓ.ም መደበኛ ትምህርት እንደሚጀምር ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ይሁን እንጅ በአማራ ክልል በተከሰተው የጸጥታ ችግር ምክንያት አሁንም ወደ መማር ማስተማር ሂደት ያልገቡ አካባቢዎች ይገኛሉ።

ከእነዚህና አካባቢዎች መካከል ሰሜን ወሎ ዞን አንዱ ነው፡፡ በዞኑ አብዛኛ አካባቢዎች የመማር ማስተማር ሥራው እየተከናወነ ቢሆንም አሁንም በጽጥታ ችግር ምክንያት ትምህርት ያልተጀመረባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን የሰሜን ወሎ ዞን አሥተዳዳሪ አቶ አራጌ ይመር ገልጸዋል፡፡ አሥተዳዳሪው እንዳሉት ከአጠቃላይ በዞኑ መመዝገብ ከሚገባቸው ተማሪዎች ውስጥ 68 በመቶ አንደኛ ደረጃ እና 50 በመቶ ደግሞ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ተመዝግበው በመማር ላይ ይገኛሉ። ቀሪ ተማሪዎችን በአጭር ጊዜ ወደ ትምህርት ቤት እንዲመለሱ ለማድርግ ከትምህርት ባለሙያዎች እና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር በመቀናጀት የቅስቀሳ ሥራ እየተሠራ ይገኛል፡፡

በአካባቢው የሚገኘው ኮማንድ ፖስትም ከጸጥታ ማስከበር ሥራው በተጓዳኝ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እንዲገቡ እየሰራ ይገኛል ብለዋል ዋና አስተዳዳሪው፡፡ አሁን ላይ 90 በመቶ መምህራንም መደበኛ ሥራቸው ላይ መኾናቸውን ያነሱት አሥተዳዳሪው ቀሪ መምህራን ወደ ሥራ ቦታቸው እንዲመለሱ ጥሪ መደረጉን አንስተዋል፡፡ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለሚገኙ ተማሪዎችም የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል ተብሏል፡፡

ወላጆች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና በየደረጃው የሚገኙ አደረጃጀቶችም ለሰላም ዘብ እንዲቆሙ እና ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ኅላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል፡፡ በዞኑ 387 ሺህ 794 ተማሪዎች ለመመዝገብ መታቀዱንም ከዞኑ ትምህርት መምሪያ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተደዳር ሁለት ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በኩታገጠም የስንዴ ሰብል ለምቷል።
Next article“ሰላም እና መረጋጋት ላይ ካልተሠራ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴው ይረጋጋል ብሎ ማሳብ አስቸጋሪ ነው” ፋንታሁን ባይሌ (ዶ.ር)