በዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተደዳር ሁለት ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት በኩታገጠም የስንዴ ሰብል ለምቷል።

22

ሰቆጣ፡ መስከረም 26/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዋግኽምራ ብሔረሰብ አሥተደዳር ግብርና መምሪያ ከ1ሽህ 8 መቶ ሄክታር በላይ መሬት በኩታገጠም የስንዴ ሰብል መሸፈኑን አስታውቋል፡፡ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር በ2015/16 የመኸር እርሻ በኩታ ገጠም የተዘራ ስንዴ ማሳ የመስክ ምልከታ ተካሂዷል።
በመስክ ምልከታው የወረዳና ከተማ አስተዳደር የግብርና ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈውበታል፡፡

አርሶ አደር ቄስ መብራት ዳምጤ በሰቆጣ ዙሪያ ወረዳ የሳይዳ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ አርሶ አደሩ በዘንድሮው የመኸር እርሻ ሶስት ጥማድ የሚደርስ መሬታቸውን በስንዴ ሸፍነዋል፡፡ በኩታ ገጠም መዝራታቸው ለተባይ ቁጥጥሩ ምቹ እንደነበረ ተናግረዋል፡፡ ምርታማነትን የሚጨምር እንደኾነም ያነሳሉ፡፡
በዘንድሮው መኽር እርሻ ከ16 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁም ተናግረዋል።

አርሶ አደር ደባሽ ተፈሪ በደሃና ወረዳ ጭላ ቀበሌ ነዋሪ ናቸው፡፡ ሶስት ጥማድ የእርሻ መሬታቸውን ስንዴ ዘርተዋል። ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ተጠቅመዋል፡፡ በኩታገጠም መዝራታቸው ውጤታማ እንደሚያደርጋቸው ተናግረዋል፡፡ ካሁን ቀደም ግብዓት ሳይጠቀሙ በተናጠል በመዝራታቸው ከሶስት ጥማድ መሬት ላይ አራት ኩንታል ያልበለጠ ምርት ያገኙ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ አርሶ አደሩ አሁን ከ20 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚያገኙ ገልፀዋል።

የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ግብርና መምሪያ ኀላፊ አቶ አዲስ ወልዴ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ ስንዴን በኩታገጠም መዝራት ልምድ እየተደረገ መምጣቱን ተናግረዋል። ባለፈው ዓመት ስንዴን በኩታገጠም ተሸፍኖ ከነበረው 774 ሄክታር መሬት በዘንድሮው መኸር እርሻ ወደ 1 ሽህ 805 ሄክታር መሬት ማደጉን ተናግረዋል። በዘንድሮው የመኸር እርሻ የክረምት ዝናብ ዘግይቶ ቢጀምርም የአርሶ አደሮች እርሻን በኩታ ገጠም መሸፈን ያለውን ጠቀሜታ በመረዳታቸው የተሳታፊ አርሶ አደሮች ቁጥር መጨመሩንም አቶ አዲስ ገልፀዋል። ስንዴን በኩታገጠም በማረስ ምርታማነትን በማሳደግ በሄክታር እስከ 26 ኩንታል ምርት እንዲያገኙ ለማስቻል እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡አጠቃላይ በኩታ ገጠም በተዘራው የስንዴ ሰብል 61ሽህ 6 መቶ ኩንታል ምርት ይጠበቃል ብለዋል ኃላፊው።

ዘጋቢ፦ ሰሎሞን ደሴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በቀጣዩ የመስኖ ሥራ እንቅስቃሴ ላይ በሥፋት በመሳተፍ ሊከሰት የሚችለውን የምግብ እጥረት ለመቅረፍ እንሠራለን” የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ
Next articleተማሪዎችን ወደ መደበኛው የትምህርት ገበታ ለመመለስ ማኅበረሰቡ ኅላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ ቀረበ፡፡