
ባሕር ዳር: መስከረም 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የሀገሪቱ የምጣኔ ሀብት መሠረት እንደኾነ የሚዘመርለት ግብርና አሁን ላይ ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ፈተናው በርክቷል።
ሰው ሠራሽ የአፈር ማዳበሪያ እጥረት እና የጸጥታ ችግር በተጨማሪ የሰብል በሽታና አውዳሚ ተባይ ተከስቷል።እነዚህ እንቅፍቶች በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ተከስተው በመኸር ሰብል ምርት ላይ ከወዲሁ ጥላቸውን አጥልተዋል።
ሊያጋጥም የሚችለውን የምርት እጥረት ማካካስ የሚቻለው በመጭው የመስኖ ሥራ እንቅስቃሴ ላይ በሰፊው በመሳተፍ ነው፡፡
በጉዳዩ ላይ የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት እያደረገ ነው።
በ2016 የመስኖ ሥራ በዞኑ ከ31 ሺህ ሄክታር በላይ ማሣ ለማልማት ታቅዷል። የመምሪያው ኀላፊ ታደሰ ማሙሻ ከዚህ ውስጥ 29 ሺህ ሄክታር ማሣ በስንዴ ይለማል ተብሎ መታቀዱንም ተናግረዋል።
በችግር ውስጥ ብንኾም ምርት ማምረት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነዉ ብለዋል ኀላፊው። የተፈጥሮ ማዳበሪያ መጠቀም ትኩረትን የሚሻ ጉዳይ መኾኑንም ነው የጠቆሙት፡፡
በሥራው ላይ ርብርብ በማድረግ ሊፈጠር የሚችለውን የምግብ አቅርቦት እና የዋጋ ውድነት መቀልበስ እንደሚስፈልግም ገልጸዋል፡፡
የምግብ ዋጋ እንዳይጨምር ትኩረት ተሠጥቶ ሊሠራ እንደሚገባ ኀላፊው ተናግረዋል፡፡
አስከፊ ችግር ከመምጣቱ በፊት ኹሉም በሥራው ላይ በመሳተፍ ያሉ አማራጮችን በመጠቀም ለችግሮች መፍትሔ መስጠት እንደሚገባ ኀላፊው ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ለዓለም ለይኩን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!