
ባሕር ዳር: መስከረም 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከ72 ሺህ በላይ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ማግኘታቸውን የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አስታውቋል።
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ምጥን ብርሃኑ በጎ አድራጎት ማኅበራት የትምህርት ቁሳቁስን ለማሰባሰብ እያደረጉት ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
ድጋፍ የሚደረግላቸው ወገኖችም በሌሎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘርፎች እንዲሰማሩ እየተደረገ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
እድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ሕጻናት በትምህርት ቁሳቁስ ችግር ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው እንዳይስተጓጎሉ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም ወይዘሮ ምጥን ጠቁመዋል፡፡ በሕጻናት ላይ የሚሠሩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በንቅናቄ መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ሴቶች ሕጻናት እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ ወርዶ ሕጻናትን ለመደገፍ እየተሠራ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡
በጎ አድራጎት ማኅበራትን፣ በሕጻናት እና በእናቶች ላይ የሚሠሩ ድርጅቶችን፣ ባለሃብቶችን እና ማኅበረሰቡን በማሳተፍ ለተማሪዎች ደብተር፣ እስከረቢቶ፣ እርሳስ፣ የተማሪዎች የደንብ ልብስ፣ ጫማ እና የደብተር መያዣ ቦርሳ ማሰባሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
እስካሁንም፡-
👉74 ሺህ 939 ደርዘን ደብተር
👉13 ሺህ 693 ፓኬት እስክርቢቶ
👉10 ሺህ እርሳሶች
👉2 ሺህ 113 የደብተር መያዣ ቦርሳዎች
👉3 ሺህ 882 የተማሪዎች የደንብ ልብስ
👉120 ጫማዎች
👉120 ሸሚዞች
👉ከ11 ካርቶን በላይ ሳሙና አንጻራዊ ሰላም ባለባቸው 12 ዞኖች መሰብሰብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
72 ሺህ 732 ተማሪዎች የትምህርት ድጋፍ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል፡፡ ድጋፉ እንደ ከተሞቹ ሥፋት እና አቅም የሚወሰን እንደኾነ ያነሱት ኀላፊዋ በቀበሌ፣ በክፍለ ከተማ እና በወረዳ ተደራጅቶ እንደሚሠጥም ተናግረዋል፡፡
ሃብቱ በሕጻናት ላይ ከሚሠሩ በጎ አድራጎት ማኅበራት፣ ከረጅ ድርጅቶች፣ ከመረዳጃ ማኅበራት እና ቅን ልብ ካላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች የተሰበሰበ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
የቆዩ እሴቶች እየዳበሩ በመምጣታቸው በተደራጀ መንገድ ከሚደረጉ ድጋፎች በተጨማሪ በየሠፈሩ እና በየአካባቢው ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ለተቸገሩ ወገኖች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ ያደረጉ መኾኑንም ጠቁመዋል፡፡በተደራጀ እና በተጠና መንገድ ድጋፍ ለማድረግም ሥራዎች እየተሠሩ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ከትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በተጨማሪ ቋሚ ድጋፍ የሚያገኙ ሕጻናት መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ወይዘሮ ምጥን እንዳሉት ቋሚ ሥራ እንዲኖራቸው በማድረግ ሕጻናት ሳይቆራረጥ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ማኅበረሰቡ የቀደመ እሴቱን በመጠቀም አንድ ደብተር ለአንድ ተማሪ በሚለው መርህ መሠረት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይስተጓጎሉ ማድረግ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ማፍራት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ዛሬ ሕጻናት ላይ መሥራት ካልተቻለ ነገ ሀገር በምትፈልገው መንገድ ትውልድ መገንባት አይቻልም ነው ያሉት፡፡ የነገ ሀገር ተረካቢ የሆነውን ትውልድ በእውቀት እንዲታነጽ ማድረግ ቀዳሚ ሥራ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡
ከትምህርት ገበታቸው የሚርቁ ሕጻናትን በባለቤትነት ስሜት መቆጣጠር የማኅበረሰቡ ድርሻ መኾኑንም የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊዋ ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!