
ደባርቅ: መስከረም 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን የመኸር ዝናብ ዘግይቶ በመጣሉ እና ፈጥኖ በማቆሙ ድርቅ ተከስቷል። የተከሰተውን የድርቅ አደጋ ተከትሎም አርሶ አደሮች ለችግር መጋለጣቸውን አሚኮ በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
ለጊዜውም ቢኾን በመንግሥት እና በሌሎች ቅን ልብ ባላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች እርብርብ አስቸኳይ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ወገኖች ለማገዝ ጥረቱ አሁንም እንደቀጠለ ነው ተብሏል፡፡
በተለይም በሰሜን ጎንደር ዞን ባሉ አራት ወረዳዎች የተከሰተው ድርቅ በርካታ ዜጎችን ለችግር በመዳረጉ መንግሥት፣ ማኅበረሰቡ እና ግብረሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ሲደረግ ቆይቷል፡፡
ዜጎቹ አሁን ላይ በመጠኑም ቢኾን እገዛ እየተደረገላቸው ቢኾንም በቂ እና ዘላቂ ሊኾን እንድሚገባ ነው የሚናገሩት፡፡ ሀሳባቸውን ለአሚኮ ያጋሩ የችግሩ ተጋላጮች ከሚደረግላቸው ድጋፍ ባሻገር ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በመስኖ ልማት ራሳቸውን እንዲችሉ ሁኔታዎች እንዲመቻቹላቸው ነው የጠየቁት፡፡
የሰሜን ጎንደር ዞን በበኩሉ በድርቁ ምክንያት የተጎዱ ወገኖች አሁንም የሚደረግላቸው ድጋፍ እንዲቀጥል ጠይቋል፡፡ የዞኑ ግብርና መምሪያ ኀላፊ ጌታቸው አዳነ እንደነገሩን በዞኑ አራት ወረዳዎች ድርቁ የከፋ ጉዳት በማስከተሉ ድጋፍ ማድረግ አስፈልጓል፡፡
ከሚደረገው ዕለታዊ ድጋፍ ባሻገር አርሶ አደሮች በዳግም ልማት ሥራ እንዲሰማሩ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑ ነግረውናል፡፡ “ድርቁ ያስከተለውን ጉዳት በመሥኖ ልማት ለማካካስ ጥረት እየተደረገ ነው” ተብሏል።
ኅላፊው እንዳሉት ለችግር የተጋለጡ አርሶ አደሮችን ራሳቸውን ለማስቻል በመስኖ ልማት ሥራ በስፋት ለማሳተፍ እየተሠራ ነው፡፡
766 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ሊለማ እንደሚችል በጥናት መለየቱንም ገልጸዋል፡፡ በዚህም 7 ሺህ 73 አርሶ አደሮች እንዲሳተፉ ለማድረግ እየተሠራ ነው፡፡
570 ኩንታል የስንዴ ምርጥ ዘር ፣10 ኩንታል የጤፍ ምርጥ ዘር፣ 1 ሺህ 100 ኪሎ ግራም የአትክልት ዘር እና 1 ሺህ 462 ዩሪያ እና ዳፕ ማዳበሪያ ለመስኖ ሥራው እንደሚያስፈልግ መምሪያ ኀላፊው ገልጸዋል፡፡
የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ተለይተው ለግብርና ቢሮ መቅረባቸውን እና በግብርና ቢሮ በኩልም አስፈላጊው እገዛ እንደሚደረግ መገለጹን አስረድተዋል፡፡
መንግሥት ከሚያደርገው ድጋፍ ባለፈም እነዚህን ዜጎች ለመርዳት የሚፈልግ ግብረሰናይ ድርጅት ሁሉ አስፈላጊውን እገዛ በማድረግ ዜጎቹን ከችግር ማውጣት እንደሚገባ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!