
ባሕር ዳር: መስከረም 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ከስድስት አስርት ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የአፍሪካ ሀገራት ትልቁ የስፓርት ሁነት እንደ ምዕራባዊያን የዘመን ቀመር የ2023 የውድድር መድረኩን ሊከፍት 99 ቀናት ብቻ ቀርተውታል።
በ54 ሀገራት የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድኖች መካከል በማጣሪያ ረጅም እና ፈታኝ ውጣ ውረዶችን ቋጭቶ 24 ተሳታፊ ብሔራዊ ቡድኖች ለተጨባቂው ክስተት ተለይተዋል ቀርበዋል።
የ2023 የአህጉራዊው ውድድር ተረኛ አስተናጋጅ ሀገር ደግሞ ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ኮትዲቯር ናት።
ሀገሪቷ ውድድሩን የማስተናገድ እድሉ ከተሰጣት ጊዜ ጀምሮም ለዝግጅቱ ድምቀት ጠብ እርግፍ ስትል ቆይታለች ተብሏል።
ኮትዲቯር የአፍሪካ አህጉር የእግር ኳስ ቤተሰቡ እና ወዳጆች ዐይን ማረፊያ ይሆናል የተባለውን ውድድር በስኬት አስተናግዳ ለመሸኘት የምታደርገው ጥረት በብዙዎች ዘንድ ምስጋና እየተቸረው ነው።
ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ኮትዲቯር ከስታዲየሞች ማሻሻያ እና ግንባታ እስከ አስፈላጊ መሠረተ ልማቶች ግንባታ ድንቅ የተባለለት ዝግጅቷ እየተጠናቀቀ የእንግዶቿን መምጣት ብቻ ትጠባበቃለች ተብሎላታል
አህጉራዊው ውድድር ግብጽ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ከተካፈሉበት ታሪካዊው የ1957ቱ የመጀመሪያ ውድድር ጀምሮ እስካሁን ድረስ 33 ጊዜ ተከውኗል። በመድረኩ አዳዲስ አስተናጋጅ እና አሸናፊ ሀገራትን ተመልክተንበታል።
ተወዳጁ የአፍሪካ ዋንጫ የስድስት አስርት ዓመታት ታሪካዊ ሂደቱ ምን ይመስላል?
ተወዳጁን አህጉራዊ ውድድር በጊዜ መነጸር አመጣጡን ስንመለከት ከ1950 እስከ 1960 የነበሩት ዓመታት የውድድር መድረኩ የጅማሮ ዓመታት ኾነው እናገኛለን። ከሦስት ተሳታፊ ሀገራት ወደ አምስት ተሳታፊ ሀገራት ከፍ ያለበትም ጊዜ ነበር። ቱኒዝያ እና ናይጀሪያ በወቅቱ የነበሩትን ተሳታፊ ሀገራት ተቀላቀሉ።
እንደ ጎርጎሮሳዊያኑ የዘመን ስሌት ከ1960 እስከ 1970 ያለት ዓመታት ደግሞ የምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ጋና የውድድር መድረኩ ባለክብርነት ጎልቶ የወጣበት ወቅት ነበር። 1963 የመጀመሪያ ተሳትፏቸውን ያደረጉት “ጥቋቁር ከዋክብቱ” ዋንጫውን ሲያነሱ በተጨማሪም ሁለት ጊዜ ለፍጻሜ በቅተዋል።
ከ1970 እስከ 1980 ድረስ ስድስት ብሔራዊ ቡድኖች የውድድሩን ዋንጫ አሳክተዋል። ከነዚህ ሀገራት መካከል ሱዳን፣ ኮንጎ ብራዛቪል እና ሞሮኮ ይገኙበታል።
ወደ 1980ዎቹ ዓመታት በምዕናብ ስናቀና ካሜሮን የአህጉራዊው ውድድር ድምቀት እና ክስተት ኾና እናገኛለን። ሦስት ጊዜ ለፍጻሜ ደርሰው በ1984 እና በ1988 የውድድሩን ዋንጫውን ከፍ አድርገው አጣጥመዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1992 ጀምሮ የተሳታፊ ሀገራት ቁጥር ወደ 12 ከፍ ብሏል። እስከ ምዕራባዊያኑ ሚሊኒየም መግቢያ ድረስም ደቡብ አፍሪካ በውድድር መድረኩ የተሻለች ሀገር ሆና ብቅ ብላ ነበር።
ከአዲሱ ምዕተ ዓመት ጀምሮ ሰሜን አፍሪካዊቷን ሀገር ግብጽ የሚተካ አልተገኘም። ለተከታታይ ሦስት ጊዜ በ2006፣ 2008 እና 2010 ፈርኦኖቹ በመድረኩ የነገሱ ቀዳሚ ብሔራዊ ቡድኖች ሆነው አልፈዋል።
እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ2010 ጀምሮ የአፍሪካ ዋንጫ ከአጋር አካላት ጋር በተደረገ ስምምነት ዳጎስ ያለ ገንዘብ የሚገኝበት ኾኖ መጥቷል።
የአህጉሩ ዋንጫ ሌላኛው ምዕራፍ 2019 ላይ ይጀምራል።
በ2017 የወቅቱ የካፍ ፕሬዝዳንት የነበሩት አህመድ አህመድ የውድድር ጊዜው ከጥር ወደ ሰኔ እንዲመጣ ያደረጉት ያልተሳካ ጥረት ተጠቃሽ ነበር። ከዚህ ባለፈ ግን የተሳታፊ ሀገራት ቁጥር ከ16 ወደ 24 እንዲያድግ የቀድሞው የካፍ ፕሬዝዳንት የላቀ አሻራ አርፎበታል።
የ2019ኙን ግብጽ እና የ2021ዱን ውድድር ካሜሮን አስተናግደው አሁን ደግሞ ለተረኛዋ ሀገር ኮትዲቯር አስረክበዋል።
24 ብሔራዊ ቡድኖች በአምስት ከተሞች በሚገኙ ስታዲየሞች ተጠባቂውን ፍልሚያ ያካሂዳሉ። እስከ አሁን ድረስም ከ500 ሚሊዮን በላይ ተመልካቾች ውድድሩን እንደታደሙት የካፍ ኦንላይን መረጃ ያሳያል።
አህጉራዊ ውድድሩን ለማስተናገድ ኅላፊነቱን የወሰደው የአላስኔ ኦውታራ መንግሥት ለውድድሩ ያደረገውን ዝግጅት የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን የበላይ ጠባቂ ፓትሪስ ሞትሴቤ አሞግሰዋል። ምስጋናቸውንም አቅርበዋል።
የሀገረ ኮትዲቯር ዋና ከተማ መናገሻ እና የምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ መዳረሻ የሆነችው አቢጃን ሁለት ስታዲየሞች ተዘጋጅተውባታል። የመክፈቻ እና የመዝጊያ ጨዋታዎች የሚከናወኑበት 60 ሺህ ተመልካች የመያዝ አቅም ያለው የአላስኔ ኦውታራ ስታዲየም አንዱ ነው።
ለውድድሩ ተብሎ በብዙ መልኩ እድሳት የተደረገበት የፌሊክስ ቦጊኒ ስታዲየምም መገኛው አቢጃን ናት። 29 ሺህ ታዳሚዎችን እንዲይዝ ተደርጎ በድጋሜ ተዘጋጅቷል ተብሏል።
የ1984ቱን የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ የማስተናገድ እድል የነበረው ቦኬ ከተማ ላይ የሚገኘው የዲ ላ ፔክስ ስታዲየም እና መሠረቱን በኮርሆጎ ከተማ ያደረገው የአማዱ ጎን ኩሊባሊ ስታዲየምም ዝግጁ ኾኗል ተብሏል።
በተጨማሪም የሀገሪቱ የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት በነበሩት ቻርልስ ኮናን ባኒ ሥም የተሰየመው ስታዲየም መቀመጫውን የኮትዲቫር የፓለቲካ እና አስተዳደር መናኾሪያ በሆነችው ያማሶክሮ ከተማ ነው።
ስድስተኛው የውድድሩ አስተናጋጅ ስታዲየም የዓለማችን የካካዋ ምርት መዳረሻ ወደብ በሆነችው ሳን ፔድሮ ከተማ ላይ ይገኛል። ላውረንት ፓኮ የስታዲየሙ ስያሜ ነው።
ይህ ሁሉ ቅድመ ዝግጅት ታዲያ ከአህጉራዊው የእግር ኳስ የበላይ ጠባቂ ካፍ ይሁንታ እና ምስጋና ተችሮታል። ከ99 ቀናት በኋላ በየሀገራቸው ሰንደቅ ዓላማ ያሸበረቁ የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድኖች እና የእግር ኳሱ ዓለም ከዋክብት ማረፊያቸው ኮትዲቯር ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
ውድድሩ ከጥር 13 እስከ የካቲት 11/2023 ድረስ እንደሚቆይም የወጣው መርሐ ግብር ያመለክታል። በታሪክ ለሁለተኛ ጊዜ መድረኩን የምታስተናግደው ኮትዲቯርም የአዘጋጅነት እድሉን ለሀገራዊ ልማት እና እድገት እንደምትጠቀምበት ይታሰባል።
መረጃው የካፍ ኦንላይን ድረገጽ ነው።
በሐናማርያም መስፍን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!