የኢትዮጵያን የታክስ አሥተዳደር ለማዘመን የዓለም ባንክ ድጋፍ እንደሚያደርግ ተገለጸ።

42

ባሕር ዳር: መስከረም 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያን የታክስ አሥተዳደር ለማዘመን በሚደረገው ጥረት የዓለም ባንክ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጿል።

የገቢዎች ሚኒስቴር እና የዓለም ባንክ ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች “የኢትዮጵያን የታክስ አሥተዳደር በማዘመን ወጪ ቆጣቢና ውጤታማ አገልግሎት መስጠት” በሚል ማዕቀፍ በሚተገበር የፕሮጀክት ሃሳብ ላይ ተወያይተዋል።

ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያን የታክስ ገቢ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ጋር ያለውን ጥምርታ ለማሳደግ ያግዛል ተብሏል። የኢትዮጵያን የታክስ ፖሊሲ መሠረት በማድረግ የሪፎርም ሃሳቦችን የማመንጨት፣ ቀልጣፋ፣ ዘመናዊና ተደራሽ የታክስ አሥተዳደር ሥርዓትን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት በቴክኖሎጂ የመሳለጥ፤ እንዲሁም ለታክስ ከፋዮች የሚሰጡ አገልግሎቶች የጥራት ደረጃዎች የማሻሻል እርምጃዎችን እንደሚያካትት ታውቋል።

የገቢዎች ሚኒስትር አይናለም ንጉሤ ፕሮጀክቱ ከፌደራል ባሻገር በየደረጃው በክልሎች በሚገኙ የታክስ ሰብሳቢ አደረጃጀቶች ላይ በወጥነት መተግበር አለበት ብለዋል።

የፕሮጀክቱ ዓላማዎች ከኢትዮጵያ የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ እና የመካከለኛው ዘመን የልማትና ኢንቨስትመንት ዕቅድ ጋር መጣጣም እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

በተጨማሪም በፕሮጀክቱ የዲዛይን ምዕራፍ እስከ አሁን የታክስ ሥርዓቱን ለማዘመን የተከወኑ እመርታዎች እና አበረታች ጅማሬዎች ተገምግሞ መካተት እንደሚገባቸው ተጠቅሷል። የሥራ ድግግሞሽ እና የሃብት ብክነት እንዳይከሰት የኢትዮጵያን የታክስ አሥተዳደርን ለማዘመን ሌሎች የልማት አጋር አካላት እየሠሯቸው ካሏቸው ሥራዎች ጋር መቀናጀት አለባቸው ብለዋል።

የፕሮጀክት ዲዛይኑን በበቂ የሃሳብ ግብዓቶች ለማዳበር የገቢዎች ሚኒስቴር እና የዓለም ባንክ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ የተለያዩ አውደ ጥናቶች እንደሚካሄዱ መታወቁን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸው ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይኾኑ ኅብረተሰቡ ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል” የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ትምህርት መምሪያ
Next articleታላቁ አህጉራዊ ውድድር 99 ቀናት ብቻ ቀርተውታል።