
ሁመራ: መስከረም 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሰሜን አርማጭሆ ወልቃይት ጠገዴ እና አካባቢው በጎ አድራጎት ማኅበር በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ለሚገኙ የኢኮኖሚ አቅም ውስንነት ላለባቸው ተማሪዎች የደብተር ድጋፍ አድርጓል።
የማኅበሩ ሰብሳቢ ሻለቃ ሙሉቀን አበበ በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ለሚገኙ ተማሪዎች ከ55 ሺህ ብር በላይ ወጭ በማድረግ 76 ደርዘን ደብተር ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል። ማኅበሩ በማዕከላዊ ጎንደር ዞንና በምዕራብ ጎንደር ዞን ለሚገኙ ተማሪዎች ድጋፍ ማድረጉን ነው የገለጹት የማኅበሩ ሰብሳቢ።
የደብተር ድጋፉ ለ200 ተማሪዎች እንዲደርስ ታስቦ ከዞኑ ትምህርት መምሪያ ጋር ርክክብ መደረጉን የገለጹት የማኅበሩ ሰብሳቢ በቀጣይ ማኅበሩ ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
ማኅበሩ የመማር ማስተማር ሂደቱ ውጤታማ እንዲኾን ሲደግፍ መቆየቱን ያስታወሱት ደግሞ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ገብረ ማርያም መንግሥቴ ናቸው።
አሁን ላይ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸው ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው እንዳይርቁ ለማድረግ ማኅበሩ የደብተር ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።
በዞኑ ከ6 ሺህ 500 በላይ ተማሪዎች የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸው በመኾኑ ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዳይኾኑ ድጋፉ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ያሉት ኀላፊው ማኅበሩ ላደረገው ድጋፍም ምሥጋናቸውን አቅርበዋል።
ዞኑ ያለ በጀት የሚንቀሳቀስ በመኾኑ በርካታ የትምህርት መስጫ ቁሳቁስ እጥረት እንዳለም ኀላፊው ገልጸዋል።
ሌሎች ማኅበራትና አቅም ያላቸው ግለሰቦች ለዞኑ ትምህርት ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!