
ባሕር ዳር: መስከረም 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የዋግ ልማት ማኅበር በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ጋዝጊብላ ወረዳ ለሚገኙ ትምህርት ቤቶች 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው የትምህርት ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ።
ልማት ማኅበሩ ድጋፉን ያደረገው ከግብረ ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመተባበር በሰሜኑ ጦርነቱ ወቅት ጉዳት የደረሰባቸውን ትምህርት ቤቶች መልሶ ለማቋቋም እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ መኾኑን የልማት ማኅበሩ ምክትል ዳይሬክተር ሙላው ደምሴ በርክክቡ ሥነ-ሥርዓት ላይ ገልጸዋል።
በዚህም ልማት ማኅበሩ በጋዝጊብላ ወረዳ ለሚገኙ አራት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው የትምህርት ቁሳቁሶች ማመቻቸቱን ገልጸዋል።
ከድጋፉ ውስጥ 400 የተማሪዎች መቀመጫ ወንበር፣ 40 ወንበርና ጠረጴዛ፣ 40 ጥቁር ሰሌዳ፣ አራት ኮምፒተርና አራት ፕሪንተር እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።
ልማት ማኅበሩ በብሔረሰብ አሥተዳደሩ የሚስተዋሉ የልማት ክፍተቶችን አጋር አካላትን በማስተባበር እየሠራ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
የብሔረሰብ አሥተዳደሩ ትምህርት መምሪያ ኀላፊ ሰይፈ ሞገስ በዋግ ልማት ማኅበር አስተባባሪነት ለአራት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የተደረገው የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለማቋቋም ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው ገልጸዋል።
ድጋፉ የትምህርት ግብዓቶች በመማር ማስተማሩ ሥራ ተፈጥሮ የነበረውን ችግር እንደሚያቃልል ተናግረዋል።
በድጋፍ ርክክብ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የሥራ ኀላፊዎችና ተማሪዎች እንዲሁም የተማሪ ወላጆች መገኘታቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!