“መንግሥት በምክክር ሂደቱ የሚደረስባቸውን መግባባቶች ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መኾኑን ማረጋገጡ ኮሚሽኑ የጀመራቸውን ተግባራት ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል ምቹ ኹኔታ የሚፈጥር ነው”

49

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

ባሕር ዳር፡ መስከረም 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ ያደሩ ችግሮችን ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ለመፍታት የተቋቋመ ነው፡፡ ኮሚሽኑ ሀገራዊ ምክክር ለማድረግ የሚያስችሉትን ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ሳምንታዊ ዓበይት ክንውኖችን በተመለከተ መግለጫ አውጥቷል፡፡ ከሚሽኑ በመግለጫው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የምክክር ሂደት ተሳታፊዎችን የመለየቱን ተግባር አጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያለው፡፡

እጅግ መሠረታዊ በኾኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አካታችና አሳታፊ የኾነ ምክክር በማከናወን መግባባት ላይ ለመድረስ ኮሚሽኑ በተሳታፊዎች አማካኝነት ተወካዮችን እያስመረጠ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡ ይህንኑ ተግባር አጠናክሮ በመቀጠል ተሳታፊዎችን የመለየትና የማስወከል ሥራ ባልተከናወነባቸው ክልሎች የተለያዩ ተግባራትን በማከናወን ላይ እንደሚገኝም ገልጿል፡፡

ኪሚሽኑ በአፋር እና በኦሮሚያ ክልሎች ተሳተፊዎችን በመለየት ሂደት በቅንጅት የሚሠሩ ተባባሪ አካላትን በመለየት ስልጠና ለመስጠት የዕቅድ ዝግጅቱን ማጠናቀቁንም አስታውቀዋል። በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያም የውክልና ሂደቱ ባልተናቀቀበት ደቡብ ኦሞ ዞን የማጠቃለያ ሥራ ለመሥራት ባለሙያዎቹ ወደ ስፍራው ማቅናታቸውንም አመላክቷል፡፡ በአማራ፣ በሶማሌ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና በትግራይ ክልል ሂደቱን ለማከናወን የሚያስችሉ ቅድመ ዝግጅቶችን እያከናወነ እንደሚገኝም አስውቋል። ከባለድርሻ አካላት ጋር መዋያየቱንም ገልጿል፡፡ ኮሚሽኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተገኙበት ከፌዴራል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጋር እስካሁን ባከናወናቸው ተግባራትና ቀጣይ ዕቅዶቹ ላይ ገንቢ ውይይት ማድረጉንም አመላክቷል፡፡ ውይይቱ በኮሚሽኑ ጥያቄ አቅራቢነት ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ሲያካሂዳቸው ከነበሩት ውይይቶች የቀጠለ መሆኑንም ገልጿል።

በውይይቱ መንግሥት እንደ አንድ የምክክሩ ሂደት ባለድርሻ አካል የኮሚሽኑን ገለልተኝነትና ነጻነት በጠበቀ መልኩ እስካሁን ሲያደርጋቸው የነበሩ ድጋፎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያረጋገጠበት መሆኑንም አመላክቷል፡፡ መንግሥት በምክክር ሂደቱ የሚደረስባቸውን መግባባቶች ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን አሳውቋል ነው ያለው ኮሚሽኑ በመግለጫው። ይህም ኮሚሽኑ የጀመራቸውን ተግባራት ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑንም አስታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከወጣቶች ማኅበራት እና በወጣቶች ላይ ከሚሠሩ ድርጅቶች ጋር መወያየቱንም ተናግሯል፡፡ በዚህም የምክክሩ ባለድርሻና ተሳታፊ መኾን የሚገባቸው ወጣቶች በቂ ግንዛቤ ኖሯቸው በሂደቱ በንቃት ለመሳተፍ እንዲችሉ ማኅበራቱና ድርጅቶቹ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ መግባባት ላይ ተደርሷል ነው ያለው፡፡

ኮሚሽኑ ከኦሮሚያ ክልል ሴቶች ጥምረት ጋር በአዳማ ከተማ ውይይት የማድረጉንም አመላክቷል፡፡ ሴቶች በሀገራዊ ምክክሩ ሂደት ላይ በንቃት እንዲሳተፉ ማኅበራቱ ግንዛቤ የመፍጠርና የማንቃት ሥራዎችን መሥራት እንዳለባቸው መግባባት ላይ መደረሱንም አስታውቋል፡፡

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleበዝናብ እጥረት እና በሌሎች ምክንያቶች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ እያደረገ መኾኑን የፌዴራል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
Next articleየሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 6ኛ ዙር 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት የፊታችን ሰኞ ይካሄዳል።