
ባሕር ዳር፡ መስከረም 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዝናብ እጥረት እና በሌሎች ምክንያቶች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ እያደረገ መኾኑን የፌደራል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታውቋል፡፡
በአማራ ክልል በዝናብ እጥረት መከሰት ምክንያት 1 ሚሊዮን ወገኖች አስቸኳይ የሰበዓዊ ድጋፍ እንደሚሹ አሚኮ መዘገቡ ይታወሳል፡፡ የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራም ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል በወቅታዊ ጉዳዮች መግለጫ በሰጡበት ወቅት በክልሉ እና ከክልሉ ውጭ በተፈጠሩ ችግሮች ተፈናቅለው ድጋፍ የሚሹ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ወገኖች አሉ ማለታቸውን ዘግበናል፡፡ በክልሉ በዝናብ እጥረት ምክንያት በሰሜን ጎንደር፣ በማዕከላዊ ጎንደር፣ ደቡብ ጎንደር፣ ሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ፣ ዋግኸምራ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር በአንዳንድ ወረዳዎች የዝናብ እጥረት ተከስቷል፡፡
በሰሜን ሸዋ ዞንም በግሪሳ ወፍ ወረራ ምክንያት ሌላ ችግር መከሰቱንም አመላክተዋል፡፡ እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ በክልሉ በዝናብ እጥረት ምክንያት አንድ ሚሊዮን ወገኖች አስቸኳይ ድጋፍ ይሻሉ፡፡ ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ለማድረግም የተሻለ ያመረቱ አርሶ አደሮች፣ ነጋዴዎች፣ ባለሀብቶች፣ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና መንግሥት ድጋፍ እንዲያደርጉ እየሠሩ መኾናቸውንም ነግረውናል፡፡
የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አታለል አቡሃይ የአማራ ክልል የዝናብ እጥረት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ወገኖች ድጋፍ እንዲደረግላቸው መጠየቁን ገልጸዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ተደጋጋሚ ችግር የሚያጋጥማቸው በመኾኑ የአደጋ ስጋት ኪሚሽኑ እንደሚያውቀውም ተናግረዋል፡፡ ዝናብ አጠር በመኾኑ አካባቢዎች ተደጋጋሚ ድጋፍ የሚደረግላቸው መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡
እርዳታ ሰጪ ተቋማት እርዳታ መስጠት ካቆሙ ወራት መቆጣራቸውን ያነሱት አቶ አታለል መንግሥት ክፍተቶችን ለመሙላት ከመጠባበቂያ መጋዘኖቹ እያወጣ ድጋፍ እያደረገ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ በሁሉም ክልሎች በድርቅ እና በጎርፍ አደጋ ለተጎዱና ጊዜያዊ የምግብ አቅርቦት ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች የቅድሚያ ቅድሚያ በመስጠት እየሠጡ መኾናቸውንም አመላክተዋል፡፡
በግጭት ምክንያት ለተፈናቁ ወገኖችም ድጋፍ መላካቸውን ነው የተናገሩት፡፡ ክልሉ አስቸኳይ ድጋፍ ያስፈልጋሉ ብሎ የለያቸውን ወገኖች እየደገፉ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ አስቸኳይ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ድጋፍ እየላኩ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡
ለአማራ ክልል ከወረታና ከኮምቦልቻ መጋዘኖች እያወጡ ድጋፍ እያደረጉ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ክልሉ ቅድሚያ ያስፈልጋቸዋል ላላቸው አካባቢዎች ሁሉ ድጋፍ ይደረጋል ነው ያሉት፡፡
የክልሉ መንግሥት በራሱ አቅም ድጋፍ እያደረገ መኾኑን የተናገሩት አቶ አታለል ከክልሉ አቅም በላይ የኾነውን የፌዴራል መንግሥት ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት የቅድሚያ ቅድሚያ ያስፈልጋቸዋል ብሎ ላሳወቃቸው ወገኖች ድጋፍ መላኩንም አመላክተዋል፡፡ የቅድሚያ ቅድሚያ ለሚያስፈልጋቸው ተብሎ ለተለዩ ወገኖች የተላከው ድጋፍ በቂ ነው ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል፡፡ ካለው ፍላጎት አንጻር በቂ አይደለም ተብሎ በተጎጂ ወገኖች አንጻር ሊነሳ እንደሚችልም ተናግረዋል፡፡
የተላኩ ድጋፎች መድረሳቸውን ክልሎች እንደሚያረጋግጡ የተናገሩት አቶ አታለል ወደ አማራ ክልል የተላከውን ድጋፍ ባለው ጸጥታ ሁኔታ ሊዘገይ የሚችልበት እድል እንዳለም ተናግረዋል፡፡ ሰብል ያላመረቱ ወገኖችን የመለየት ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡ ያጋጠሙና ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን በማጥናት ከቅድመ ጥንቃቄ ጀምሮ ሥራ እንደሚሠሩም ተናግረዋል፡፡ ከጥንቃቄ አልፈው ችግሮች ሲከሰቱ መንግሥት የክምች አቅሙን እንደሚያሳድግና ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡ አፋጣኝ ድጋፍ ለሚያስፈልጉ ወገኖች ከተቀመጡ የምግብ ክምችቶች እያወጣ ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!