“የትምህርት ቁሳቁስ ዋጋ ከአምናው ቅናሽ አሳይቷል” የተማሪ ወላጆች

43

ባሕርዳር፡ መስከረም 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የትምህርት ቤቱን በር ተሰናብተው ሲወጡ ኹሉም እየዞሩ ያዩታል፡፡ ከርመው ለመመለስ በልባቸው ተመኝተው ወደ ቤታቸው ይሄዳሉ፡፡

ከመምህሮቻቸው የተቀበሉትን የትምህርት ውጤት መግለጫ ካርድ ላይ ያመጡትን ውጤት ለወላጆቻቸው አሳይተው እንዲደሰቱ ለማድረግ ፣አሊያም ከክፍል ክፍል መዘዋወራቸውን ለወላጆቻቸው እና ለጓደኞቻቸው ለማሳየት ወደ ቤታቸው ይገሰግሳሉ፡፡

ጥቂት ቀናት በዚያ ደስታ ውስጥ የቆዩ ተማሪዎች አብዛኞቹ ወላጆቻቸውን በሥራ ለማገዝ ከወላጆቻቸው ጋር ሲወጡ ሲወርዱ ከርመዋል፡፡ ገሚሶቹ እራሳቸውን በማዝናናት ከርመዋል፡፡

መስከረም ጠብቶ ምድሪቱ በአደይ አበባ ደምቃለች ፤ፀሐይ የጋረዳትን ደመና ገልጣ ብርሃኗን ለሰው ልጆች ያለስስት እያደረሰች ነው፡፡

ተማሪዎች ትምህርት ቤት ተከፈተ የሚለውን አዋጅ ሲጠባበቁ ሰንብተዋል፡፡ የትምህርት ቤት መከፈቻ ጊዜው ደርሶ ተማሪዎች በየትምህርት ቤታቸው ተመዝግበዋል፡፡

ወላጆቻቸው የሚገዙትን ደብተር ፣እስክርቢቶ እና እርሳስ ከጓደኞቻቸው ጋር ለማወዳደር ፍላጎታቸው ጨምሯል፡፡

በግል ትምህርት ቤት የሚማሩ ተማሪዎች የተመኙትን ሳይኾን ትምህርት ቤቱ በወሰነው እና ባስቀመጠው መሠረት የሚገዛላቸው በመኾኑ ውድድሩን ቀላል አድርጎታል፡፡

ወላጆችም ልጆቻቸው ከጓደኞቻቸው እንዳያንሱ እና የሞራል ስብራት እንዳይደርስባቸው የተሻለውን ደብተር በተሻለ ዋጋ በመግዛት ልጆቻቸውን ያስደስታሉ፡፡ ቀሪዎቹ የኪሳቸውን አቅም አይተው “ዋናው መማሩ ነው” በሚል ስሜት ያገኙትን ደብተር ገዝተው ለልጆቻቸው ያበረክታሉ፡፡

ልጆችም የወላጆቻቸውን ስሜት ተረድተው በተገዛላቸው ደብተር ትምህርታቸውን ይጀምራሉ፡፡ ከሌሎች ጋር መፎካከር ለእነዚህ ተማሪዎች ቦታ የለውም፡፡ ትምህርት በሰፊው ሲጀመር ፉክክሩም እየተረሳ ይሄድ እና ዋናው ትኩረታቸው ትምህርታቸው ላይ ይኾናል፡፡

በዚህ ዓመት በሰላሙ ምክንት የትምህርት ቤቶች መከፈቻ ጊዜ ቢዘገይም በተስተካከለው የጊዜ ሠሌዳ ተጀምሯል፡፡ ወላጆችም የመማሪያ ቁሳቁስ የመግዛቱን ነገር አጠናክረው ይዘውታል፡፡

አሚኮ የትምህርት ቁሳቁሶች የሚሸጡበትን ሱቅ ተዘዋውሮ ተመልክቷል፡፡ ባለፈው ዓመት ከ65 ብር እስከ 70 ብር ሲሸጥ የነበረ ሲነርላይን ባለሁለት መሸፈኛው 50 ወረቀት ደብተር ከዝቅተኛው 40 ብር እስከ ከፍተኛው 55 ብር እየተሸጠ ተመልክቷል፡፡

ባለፈው ዓመት ከ70 ብር እስከ 80 ብር ይሸጥ የነበረው ራዲካል ባለ 50 ወረቀት ደብተር ዛሬ ላይ 53 ብር እየተሸጠ ነው፡፡

አምና ከትንሹ 20 ብር እስከ 25 ብር ይሸጥ የነበረው እስክርቢቶ በዚህ ዓመት ከ15 ብር እስከ 20 ብር እየተሸጠ ነው፡፡

ባለ ከለር እርሳስ በባኮ 60 ብር መደበኛ እርሳስ 10 ብር ማጥፊያ እንዲኹም መቅረጫ 20 ብር ይሸጣል፡፡

ባለፈው ዓመት ከ80 ብር እስከ 90 ብር ሲሸጥ የነበረ ድርብ ሽፋን ያለው ባለ ሃምሳ ወረቀት ሲነርላይን እስኩየር ደብተር 70 ብር እየተሸጠ ነው፡፡

ድርብ ሽፋን ያለው ባለ መቶ ወረቀት ደብተር 130 ብር እየተሸጠ ነው፡፡ ምንም ሽፋን ሳይኖረው የተዘጋጀ ባለ 50 ወረቀት ደብተር ዋጋው ከ40 ብር ዝቅ ማለቱን እና ሸማቹም ምንም ፍላጎት እንደሌለው መመልከት ችሏል፡፡

ደስታ ወረቀት ከአራት መቶ ሃምሳ ብር ወደ አምስት መቶ ሃምሳ ብር ማደጉንም አሚኮ በሥፍራው ተገኝቶ ተመልክቷል፡፡

ለሥዕል መሳያ እና መጻፊያ የሚፈለጉ ሲነርላይን ባለ 50 ወረቀት ደብተር ከ50 ብር እስከ 60 ብር እየተሸጠ መኾኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ወይዘሮ ሰርካለም አስማረ በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ቀበሌ 16 ነዋሪ ናቸው፡፡ ወይዘሮ ሰርካለም አራት ልጆች አሏቸው፡፡ ሁለቱ ልጆች ተምረው አጠናቅቀዋል፡፡ ለሁለት ልጆቻቸው የመማሪያ ቁሳቁስ ሲገዙ አገኘናቸው፡፡ የመማሪያ ቁሳቁስ በበቂ መጠን አንደቀረበም ተናግረዋል፡፡

ወይዘሮ ሠርካለም ባለፈው ዓመት ደብተር ባይገዙም አሁን የገዙበት ዋጋ የተጋነነ እንዳልኾነ ተናግረዋል፡፡ ለአንድ ቅድመ መደበኛ እና ለአንደኛ ክፍል ተማሪ ልጆቻቸው 7 መማሪያ ደብተር እና 4 የሥዕል ደብተር ፣እስክርቢቶ ፣እርሳስ እና ወረቀት ገዝተዋል፡፡ በአጠቃላይ 2 ሺህ 465 ብር ወጭ አድርገዋል፡፡

አቶ አበበ ስማቸው በባሕር ዳር ከተማ አሥተዳዳር የቀበሌ 14 ነዋሪ ናቸው፡፡ ለአንድ ቅድመ መደበኛ እና ለአንድ የ3ኛ ክፍል ተማሪ ልጆቻቸው ደብተር እየገዙ አገኘናቸው፡፡ የሚገዙት ደግሞ ትምህርት ቤቱ በሠጣቸው አቅጣጫ መሠረት ነው፡፡ አንድ ደርዘን ደብተር፣ ሁለት ደስታ ወረቀት ፣እስክርቢቶ ፣እርሳስ ፣የእርሳስ ማጥፊያ እና መቅረጫ የእጅ ማጽጃ እና ሶፍት ገዝተዋል፡፡ አቶ አበበ በደብተር ዋጋ አንጻራዊ ቅናሽ መኖሩንም ጠቁመዋል፡፡ የትምህርት ቁሶችም በሚፈለገው መጠን መቅረቡን ነው የነገሩን፡፡

በእስክርቢቶ ፣በእርሳስ ፣የእርሳስ ማጥፊያ እና መቅረጫ ዋጋ ላይ ጭማሬ አለመኖሩንም ተናግረዋል፡፡

አቶ አበበ የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለመፍጠር ዛሬ ለልጆቻችን ተገቢውን ነገር እያደረግን ነውም ብለዋል፡፡

ሌሎች ወላጆችም በሚፈለገው ልክ ደብተር እየገዙ በመኾኑ ኹሉም በቁርጠኝነት ለትምህርት መሠለፉን እንደታዘቡም አንስተዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እንሰራለን” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው
Next articleበዝናብ እጥረት እና በሌሎች ምክንያቶች ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ እያደረገ መኾኑን የፌዴራል አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ፡፡