“የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እንሰራለን” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው

40

ባሕር ዳር: መስከረም 25/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የከተማዋ ነዋሪዎች የሚያቀርቧቸውን የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰሩ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው ተናገሩ።

በምክትል ርእሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተሞችና መሠረተ ልማት ቢሮ ኅላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) የተመራ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኅላፊዎች ልዑክ ትናንት በባሕር ዳር ከተማ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን እና ፍብሪካዎችን የሥራ እንቅስቃሴ ተመልክተዋል፡፡

የባሕርዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው በከተማዋ የሚገኙ ፋብሪካዎች እና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ያሉበትን ደረጃ መመልከታቸውን ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ ከተማዋ አንጻራዊ ሰላም ያለባት በመኾኗ ፋብሪካዎች ሥራ ላይ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ የፋብሪካዎችን እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን የሥራ እንቅስቃሴ በመመልከት ያሉባቸውን ችግሮች መለየታቸውንም ገልጸዋል፡፡

በምልከታቸው በከተማ አሥተዳደሩ ሊፈቱ የሚገባቸውን ችግሮች መፍታት የሚያስችል ግብዓት ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ የመሰረተ ልማት ችግሮች እና የማስፋፊያ ቦታ ጥያቄዎችን በአጠረ ጊዜ ለመመለስ እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡

ሰላም ለልማት ወሳኝ ጉዳይ መኾኑን ተናግረው

በክልሉ ባለው የሰላም እጦት ኢንዱሰትረዎች ምርታቸውን ወደ ገበያ ማቅረብ አለመቻላቸውን እንደ ችግር አንስተዋል፡፡ የሰላም እጦቱ በከተማዋ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ላይ ጫና እያሳደረ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡

በከተማዋ ለሚመረቱ የኢንዱስትሪ እና ፍብሪካ ምርቶች የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ለማቅረብ የሰላም እጦቱ እንቅፋት መኾኑንም ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ተናግረዋል፡፡ ችግሮችን በውይይት በመፍታት ሰላምን ማጽናት እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል፡፡ ራሳችን በራሳችን እየጎዳን ሕዝቡን ለጉስቁልና መዳረግ የለብንም ነው ያሉት፡፡

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ሰላምን ማጽናት ካልተቻለ ክልሉን ተወዳደሪ ማድረግ እንደማይቻልም ተናግረዋል፡፡ በኢንዱስትሪ ዘርፉ የታዩ ችግሮችን በአፋጣኝ እንፈታለን ብለዋል፡፡ በከተማዋ ያለው ሰላም ዘላቂ እንዲኾን እና ሕዝብን የሰላሙ ባለቤት ለማድረግ እየተሠራ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ በከተማዋ እስከ ቀበሌ ድረስ ሕዝባዊ ውይይቶች እየተደረጉ መኾኑንም አንስተዋል፡፡ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍሎች ሰላም አስፈላጊ መኾኑን በውይይቶቻቸው እንደሚያነሱ እና ለሰላም ዘብ ለመቆም ቁርጠኞች ናቸው ብለዋል።

ሁሉም የሚስማማባቸው የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች እንዳሉ የተናገሩት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው ውስንነቶች የተፈጠሩት አፈታቱ ላይ መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ እርስ በእርስ ከመገዳደል በመውጣት ችግሮችን በንግግር እና በውይይት መፍታት ይገባልም ነው ያሉት፡፡

የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ሰላም ወዳድ ብቻ ሳይሆኾኑ ሰላም ለማስፈን የሚሠሩ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ሕዝቡ የሰላም እጦት ችግሮች እንዲፈቱ እያደረገው ያለውን ጥረት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የከተማዋን ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዎች ሊያነቃቁ እና የኑሮ ውድነቱን ሊቀንሱ የሚችሉ ሥራዎችን ከኅብረሰተቡ ጋር እየተነጋገርን እንሠራለን ነው ያሉት፡፡ “የከተማዋ ነዋሪዎች የሚያቀርቧቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች ከሕዝብ ጋር በጋራ በመኾን ለመፍታት በትኩረት እንሠራለን” ነው ያሉት።

ሕዝቡ ለአመራሩ የሚሰጠው ድጋፍ ውጤታማ ሥራ ለማከናወን ትልቅ አቅም መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ የሕዝብን ትልቅ አቅም በአግባቡ ተጠቅመው የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ ጥረት እንደሚያደርጉም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የሆቴል ቱሪዝም ለማስደግ ለ45 ባለሀብቶች በሆቴል ኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሳተፉ ፈቃድ ሰጥተናል” የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር
Next article“የትምህርት ቁሳቁስ ዋጋ ከአምናው ቅናሽ አሳይቷል” የተማሪ ወላጆች