
ደብረ ብርሃን: መስከረም 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የደብረ ብርሃን ከተማ እድገቷ እየተፋጠነ ነው፡፡ ይሁን እንጅ በከተማዋ ደረጃቸዉን የጠበቁ ሆቴሎች አለመገንባታቸዉ ከዘርፉ የሚገኘዉን ጥቅም እንደጎዳው የከተማ አሥተዳደሩ ባሕልና ቱሪዝም ተጠሪ ጽሕፈት ቤት አስታውቋል፡፡
የከተማ አሥተዳደሩ ባሕልና ቱሪዝም ተጠሪ ጽሕፈት ቤት የቅርስ ጥበቃና ቱሪዝም ቡድን መሪ አክሊል ጌታቸዉ ባለፉት ዓመታት የተገነቡት ሆቴሎች የከተማዋን እድገት ታሳቢ ያደረጉ ባለመኾናቸዉ በሁለንተናዊ እድገቷ ላይ ችግር ሲፈጥር ቆይቷል ብለዋል፡፡
ዘርፉን ብቁና ተወዳዳሪ እንዲኾን ለማስቻል ለ45 ባለሀብቶች በሆቴል ኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሳተፉ ፈቃድ መሰጠቱን ነው ለአሚኮ የተናገሩት፡፡ ቡድን መሪዉ አሁን ላይ 23 ባለሀብቶች የግንባታ ፈቃድ ወስደዉ ባለ 4 እና 5 ኮከብ ሆቴል ለመገንባት ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል፡፡
የሆቴል ቱሪዝም አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን ከደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲና ከደብረ ብርሃን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጋር በጋራ በመኾን የክህሎትና ተግባር ተኮር አጫጭር ሥልጠና መሰጠቱንም አንስተዋል፡፡
ባለፈዉ በጀት ዓመት ከሆቴል ቱሪዝም 38 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱን የጠቆሙት አቶ አክሊል በ2016 በጀት ዓመት ከዘርፉ 50 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሠራ ነዉ ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ሀብታሙ ዳኛቸዉ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!