ከደብረ ማርቆስ እስከ ባሕር ዳር ብቻ 1 ሺህ 226 ኢንዱስትሪዎች ሥራ አቁመዋል” አቶ እንድሪስ አብዱ

51

ባሕር ዳር: መስከረም 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) “ከደብረማርቆስ እስከ ባሕር ዳር ብቻ 1 ሺህ 226 የሚኾኑ አነስተኛ፣ መካከለኛ እና ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች በጸጥታ ችግር ምክንያት ሥራ ማቆማቸውን የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኅላፊ እንድሪስ አብዱ ተናግረዋል። ኀላፊው በክልሉ የተከሰተው የሰላም እጦት የኢንዱትሪና እንቨስትመንት ዘርፉን እየፈተነው መኾኑን ተናግረዋል፡፡

ኢንዱስትሪዎች ማግኘት የሚገባቸውን ግብዓት በወቅቱ ለማግኘት መቸገራቸውን እና ያመረቱትንም ምርት ለገበያ ማቅረብ አለመቻላቸውን አመላክተዋል፡፡ ቀደም ሲል ያመረቱትን ምርት ይዘው የተቀመጡ ኢንዱስትሪዎች መኖራቸውንም ገልጸዋል፡፡

በኢንዱስትሪው ላይ ጥገኛ የነበሩ ወገኖች ከሰላም መደፍረሱ በኋላ ከሥራ ውጭ መኾናቸውም ተነስቷል፡፡ የተከሰተው የሰላም እጦቱ ሁለንተናዊ ችግር ፈጥሯል ያሉት ኀላፊው አሁን ላይ የተገኘውን አንጻራዊ ሰላም በማስቀጠል ዘላቂ ለማድረግ መረባረብ እንደሚገባም መልእክት አስተላልፈዋ፡፡

ሰላም ካላ ክልሉ በርካታ የኢንዱስትሪ አቅሞች እንዳሉት የተናገሩት ኀላፊው ለሰላም መሥራት ካልተቻለ ክልሉ በምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴው እንደሚጎዳም ተናግረዋል፡፡ የሰላም እጦቱ በቀጣይ ሊፈጥረው የሚችለውን ክፍተት በመረዳት በጋራ መሥራት ይገባል ተብሏል።

የክልሉ ሕዝብ ጨዋ፣ ሰላም እና ልማት ወዳድ በመኾኑ ፋብሪካዎች ጉዳት ሳይደርስባቸው መቆየታቸውንም ተናግረዋል፡፡ በአንዳንድ የአበባ እና ፍራፍሬ ልማት ፋብሪካዎች ላይ ጉዳት ቢደርስም አብዛኛዎቹን ፋብሪካዎች ግን ሕዝቡ የእኔ ናቸው በማለት እየጠበቀ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

የማኅበሰረቡ ሀቀኝነት እና ሰላም ወዳድነት በቀጣይ አዳዲስ አልሚዎች ወደ ክልሉ ለመሳብ ትልቅ አቅም መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ መልካም ተሞክሮዎችን እያጎላን ችግሮቻችንን እያረምን ክልሉን ምቹ የኢንቨስትመንት ማዕከል ለማድረግ እየሠራ ነው ሲሉም ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በመስኖ ስንዴ ለመሸፈን በእቅድ ከተያዘው መሬት 117 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል”የግብርና ሚኒስቴር
Next article“የሆቴል ቱሪዝም ለማስደግ ለ45 ባለሀብቶች በሆቴል ኢንቨስትመንት ዘርፍ እንዲሳተፉ ፈቃድ ሰጥተናል” የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር