“በመስኖ ስንዴ ለመሸፈን በእቅድ ከተያዘው መሬት 117 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ ታቅዷል”የግብርና ሚኒስቴር

32

ባሕር ዳር: መስከረም 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በተያዘው በጀት ዓመት 3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለመሸፈን ታቅዶ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተከናወነ መኾኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

የተያዘውን እቅድ ከማሳካት አንጻር የሚያስፈልጉ ግብአቶች፣ የቴክኒክ ድጋፎች፣ የበጀት እና የእቅድ አፈጻጸም አቅምን ለማጎልበት ያለመ መኾኑም ተገልጿል።

የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ እንደ ሀገር የመስኖ ስንዴ ልማት ምርታማነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሠራ ነው።

ባለፈው ዓመት 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት በመስኖ ስንዴ መሸፈኑን አስታውሰው በዚህ ዓመት 3 ማሊየን ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለመሸፈን ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የተያዘውን ሀገራዊ የመስኖ ስንዴ እቅድ ለማሳካት የአፈር ማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘር፣ የውኃ መሳቢያ ሞተር ፓምፕ ግብአቶች ዝግጅት እየተደረገ ነው ፤ የቴክኒክ ድጋፎችም የሚደረጉ መኾኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለም መሬት፣ የውኃ እና የሰው ኀይል ያላት በመኾኑ ይህንን አቅም በአግባቡ በመጠቀም የስንዴ ምርታማነትን ለማሳደግ የተጀመረው ጥረት ይጠናከራል ብለዋል።

ሚኒስትሩ አክለውም በመስኖ ስንዴ ለመሸፈን በእቅድ ከተያዘው መሬት 117 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱንም ገልጸዋል።

የክልሎችን አቅም አሟጦ በመጠቀም እና በመቀናጀት ለሀገራዊ እቅዱ ስኬት ክትትልና ድጋፍ የሚደረግ መሆኑም አስረድተዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታዋ ዶክተር ሶፊያ ካሳ ምርታማነትን ለማሳደግ ከሚረዱ ግብዓቶች መካከል የአፈር ማዳበሪያን በወቅቱ ለማቅረብ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ገልጸዋል።

ኢዜአ እንደዘገበው የአፈር ማዳበሪያ ትልቅ ወጪ ወጥቶበት ወደ ሀገር የሚገባ በመኾኑ በስርጭት ሂደቱና አጠቃቀሙ ላይ አስፈላጊ ጥንቃቄ እንዲደረግም አሳስበዋል።

ከየክልሉ ያለውን የአፈር ማዳበሪያ ፍላጎት ተሰብስቦ የግዢ ሥራ ለመፈጸም እየተሠራ መኾኑን ገልጸዋል። ዶክተር ሶፊያ የማጓጓዣ፣ የማከማቻና የአያያዝ ሁኔታ ላይ ተከታታይ ክትትል የሚደረግ መኾኑን ጠቁመዋል።

ሚኒስቴሩ ዛሬ በጅማ ከተማ ሀገራዊ የመስኖ ስንዴ ልማት ንቅንቄ መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር አካሄዷል።

በውይይቱ ከአማራ፣ ከኦሮሚያ፣ ከሲዳማ፣ ከደቡብ ኢትዮጵያን፣ ከማእከላዊ ኢትዮጵያ፣ ከደቡብ ምእራብ ክልሎች የግብርና ቢሮ ኀላፊዎች እንዲሁም ከግብርና ምርምሮች፣ ከኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የተውጣጡ መሪዎችና ሙያተኞች ተገኝተዋል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleሰብዓዊ ድጋፍን ዓላማ ያደረገ የሕጻናት ሩጫ መዘጋጀቱን የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አስታወቀ።
Next articleከደብረ ማርቆስ እስከ ባሕር ዳር ብቻ 1 ሺህ 226 ኢንዱስትሪዎች ሥራ አቁመዋል” አቶ እንድሪስ አብዱ