
አዲስ አበባ: መስከረም 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአማራ፣ በአፋር እና በትግራይ ክልል በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉና ችግር ላይ የሚገኙ ሴቶችን መልሶ ለማቋቋም ያለመ የሕጻናት ሩጫ እደሚያካሂድ የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ገለጸ።
የሕጻናት ሩጫው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎ ሜትር ኢንተርናሽናል ውድድር አካል እንደኾነም ነው የተገለጸው።
ፖሊዮን በጋራ ጨርሰን እናጥፋ በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው የሕጻናት ሩጫ ሌሎችን ለመርዳት እሮጣለው የሚል ዓላማ እንዳለውም ተገልጿል ።
ከውድድሩ የሚገኘው ገቢ በአማራ፣ በአፋር እና በትግራይ ክልል በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉና ችግር ላይ የሚገኙ 1 ሺህ ሴቶችን መልሶ ለማቋቋም እንደሚውል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በሰጠው መግለጫ አሳውቋል።
በመርሃ ግብሩ 2 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ መታቀዱም ተነግሯል ።
የሴቶችና ማኅበራዊ ሚኒስቴር ዴኤታ ዓለሚቱ ኦሞድ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከሩጫ ባለፈ ማኅበራዊ ኀላፊነትን በመወጣትና ሰበዓዊ ተግባራትን በመፈፀም እያደረገ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መኾኑን ገልጸዋል።
በጤና ሚኒስቴር የክትባት ዘርፍ ኀላፊ መልካሙ አያሌው ታላቁ ሩጫ ፖሊዮን በጋራ ጨርሰን እናጥፋ በሚል መልእክት የተነሳው ዓላማና መርህ የተሳካ እንዲኾን የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ክትትል ያስፈልገዋል ብለዋል።
ታለቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ለማኅበራዊ ኅላፊነት እስካሁን 20 ሚሊዮን ብር አስተዋጽኦ ማድረጉም በመግለጫው ተነስቷል።
በሕዳር ወር በሚካሄደው 23ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎ ሜትር ኢንተርናሽናል ውድድር 45 ተሳታፊዎች እንደሚካፈሉበት ይጠበቃል።
ፖሊዮን በጋራ ጨርሰን እናጥፋ በሚል መርህ የሚካሄደው የሕጻናት ሩጫ በዋዜማው እንደሚካሄድ ተገልጿል።
ዘጋቢ፡- ባዘዘው መኮንን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!