
ባሕር ዳር: መስከረም 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተሞችና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)፣ የኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ፣ የአማራ ክልል ኮምዩንኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) ጨምሮ ሌሎች የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች በባሕር ዳር የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን ተመልክተዋል፡፡
የአማራ ክልል ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊ እንድሪስ አብዱ በኢትዮጵያ ታምርት ሀገራዊ ንቅናቄ በተደረጉ ውይይቶች የኢንዱስትሪዎች ዋነኛ ችግር የመሠረተ ልማት አለመሟላት መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ኢንዱስትሪዎች ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡
እንደ ኀላፊው ገለጻ በክልሉ በሰባት ከተሞች መሠረተ ልማቶችን የማሟላት ሥራ እየተሠራ ነው፡፡ የክልሉ መንግሥት ኢንዱስትሪዎች ያሉባቸውን ችግሮች ለመፍታት በየዓመቱ በጀት እየመደበ እየሠራ መኾኑንም አስታውቀዋል፡፡ በአዲሱ ዓመት በርካታ ኢንዱስትሪዎች ያሉባቸውን ችግሮች የመፍታት ሥራ ይሠራልም ብለዋል፡፡
የኀይል አቅርቦት ችግር ሰፊና ተደራራቢ መኾኑን ያነሱት ኀላፊው በ2015 በጀት ዓመት 826 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን የኀይል አቅርቦት ችግር መፈታቱን አስታውቀዋል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል አገኙ የሚባሉ ፕሮጀክቶችም በቂ ኃይል ስላላገኙ በአቅማቸው ልክ እያመረቱ አለመኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ የኃይል አቅርቦት ችግሩን ለመፍታት እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡
የአምራች ኢንዱስትሪውን የኃይል አቅርቦት ችግር ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራም ተናግረዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ የኢንዱስትሪዎችን መርታማነት ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሠራም አመላክተዋል፡፡ በዓመቱ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ወደ 62 በመቶ ለማሳደግ አቅደው እየሠሩ መኾናቸውንም አብራርተዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት መሬት የማቅረብ እና መሠረተ ልማቶችን የማሟላት ሥራ ሲሠራ መቆየቱን የተናገሩት ኀላፊው አሁን ባለሃብቶች ካሳ እየከፈሉ አምራች እንዲስትሪዎች እንዲስፋፉ አቅደን እየሠራን ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ መሬት ወስደው ወደ ምርት ያልገቡ እና ጥቂት መሬት ወስደው ምርታማ የኾኑ ባለሀብቶች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡ መሬት አጥረው የተቀመጡ ባለሃብቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ ክትትል እና ድጋፍ እንደሚደረግ ያነሱት ኀላፊው መንግሥት የሚያደርገውን ድጋፍ ችላ በማለት ውጤታማ ባልኾኑት ላይ እርምጃ እየወሰዱ መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ከ135 በላይ አምራች ኡንዱስትሪዎች ላይ እርምጃ በመወሰድ 801 ሄክታር መሬት ወደ መንግሥት ተመላሽ ኾኗል፡፡ የተመለሱ መሬቶችን ለአዳዲስ ባለሃብቶች ማስተላለፋቸውንም አስታውቀዋል፡፡
የሚያለማውን እያበረታታን ማልማት የማይችለውን ደግሞ የእርምት እርምጃዎች እየወሰድን ክልሉ ፍትሐዊ የሆነ ምጣኔ ሃብታዊ ሽግግር እና ሥርጭት እንዲኖረው እናደርጋለንም ነው ያሉት፡፡
በ2015 በጀት ዓመት ኢንቨስትመንትን በመሳብ የተሻለ አፈጻጸም ነበር ያሉት አቶ እንድሪስ ከ454 ቢሊዮን ብር በላይ ሃብት ያስመዘገቡ ከ4 ሺህ 700 በላይ አዳዲስ ኢንቨስተሮች ወደ ክልሉ መግባታቸውን አስታውሰዋል፡፡
በ2016 በጀት ዓመት ካለፈው ዓመት የተሻለ ለመፈጸም እቅድ ይዘው እየሠሩ መኾናቸውንም አስታውቀዋል፡፡ የነበሩ ልምዶችን በመጠቀም እቅዳችንን ለማሳካት እንሠራለን ብለዋል፡፡ አሁን ያለው አንጻራዊ ሰላም ወደ ዘላቂ ሰላም ከተሸጋገረ ክልሉ ተወዳደሪና ተመራጭ መኾን ይችላል ነው ያሉት፡፡
አገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል ክልሉ የተሻለ የኢንቨስትመንት ማዕከል እንዲኾን ይሠራልም ብለዋል፡፡ በበጀት ዓመቱ ከ5 ሺህ 500 በላይ ባለሃብቶችን በክልሉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ወደ ክልሉ የመሳብ ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡ ሰላሙ ከተረጋገጠና ሥራው በተጀመረበት አግባብ ከቀጠለ እቅዳቸውን እንደሚያሳኩ ያላቸውን እምነትም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!