በክረምት የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴ ከ7 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አስታወቀ።

62

ሁመራ: መስከረም 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በ2015/16 የክረምት ወቅት የተለያዩ የበጎ አድራጎት ተግባራት መከናወናቸውን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሴቶች ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ አስታውቋል። በክረምቱ የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴ ከ7 ሺህ በላይ በጎ ፈቃደኞች ተሳትፈዋል ተብሏል።

የክረምት የበጎ አድራጎት ተግባራት ማጠቃለያ የውይይት መርሃ ግብር በሁመራ ከተማ እየተካሄደ ነው፡፡ በዞኑ የሚገኙ ወጣቶችን በማሳተፍም የተለያዩ የበጎ አድራጎት ተግባራትን ማከናወን መቻሉ ተገልጿል።

በክረምት በጎ አድራጎት እንቅስቃሴ የአረጋዊያን ቤት እድሳት፣ የአዳዲስ ቤቶች ግንባታ፣ የአልባሳት ድጋፍ፣ የትምህርት ቤቶች ጥገና፣ የችግኝ ተከላ፣ የደም ልገሳ እና የተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉ በውይይቱ ተገልጿል።

በክረምት የበጎ አድራጎት ተግባራት እንቅስቃሴ ማጠቃለያ መርሃ ግብር ላይ የተገኙት የወረዳ የሥራ ኀላፊዎች የበጎ አድራጎት ተግባራት የክረምት ወቅትን ጠብቀው የሚከናወኑ ባለመኾናቸው በበጋ ወራትም ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አመላክተዋል።

የበጎ አድራጎት ተግባራትን በትኩረትና በቁርጠኝነት ልንሠራ ይገባል ያሉት ደግሞ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሴቶች ሕጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ወይዘሮ ማህደር አድማሴ ናቸው።

በውይይቱ ላይ የተገኙት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ገብረ እግዚአብሔር ደሴ የማኅበረሰብን ችግር የምንቀርፍበትና እርስ በእርስ የመደጋገፍ ባሕላችንን የምናሳድግበት በመኾኑ የበጎ አድራጎት አገልግሎትን ዓመቱን ሙሉ ልንሠራው ይገባል ነው ያሉት።

በጎነት ወቅት የማይገድበው የኅሊና ምግብ ድንቅ ሥራ ነው ያሉት ደግሞ የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን አሥተዳዳሪ አሸተ ደምለው ናቸው።

በዞኑ እየተካሄደ ያለው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የሚደነቅ መኾኑን ያነሱት አቶ አሸተ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ኀላፊነታችሁን በቁርጠኝነት ልትወጡ ይገባል ብለዋል።

ዘጋቢ ያየህ ፈንቴ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ኢትዮጵያ በንፁህ መጠጥ ውኃ ተደራሽነት የያዘችውን የ10 ዓመት ዕቅድ በማሳካት ረገድ ዋተር ኤድ ኢትዮጵያ የራሱን ድርሻ እየተወጣ ነው” የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር
Next article“በዓመቱ የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ወደ 62 በመቶ ለማሳደግ እየተሠራ ነው” አቶ እንድሪስ አብዱ