
አዲስ አበባ: መስከረም 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ዋተር ኤድ ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓዊያኑ የዘመን ቀመር ከ2023 እስከ 2028 በአምስት ዓመት የሚተገበር ፕሮግራም ስትራቴጂክ ዕቅዱን ለባለድርሻ አካላትና አጋር ድርጅቶች ይፋ አድርጏል።
ድርጅቱ ላለፉት 31 ዓመታት በንፁህ መጠጥ ውኃ እና ንፅህና አጠባበቅ ዙሪያ ኅብረተሰቡን ሲያገለግል የቆየ ነው።
በኢትዮጵያ የዋተር ኤድ ኢትዮጵያ ዳይሬክተር ያዕቆብ መተና ዋተር ኤድ ኢትዮጵያ በክልል ከተሞች በአማራ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በትግራይ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና ሐረሪ እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር የንፁህ መጠጥ ውኃ፣ የአካባቢ ፅዳት እና የጤና አጠባበቅ ዙሪያ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
አገልግሎቱም ከስድስት ሚሊዮን በላይ ለሚኾኑ የኀብረተሰብ ክፍሎች መድረሱን ነው ያስገነዘቡት፡።
ድርጅቱ እስከዛሬ ያሳካቸውን ውጤቶች በማጠናከር የ10 ዓመት ስትራቴጂውን እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ዘመን ከ2022 እስከ 2032 ተግባራዊ እንደሚያደርግ ነው ያብራሩት፡፡
ዳይሬክተሩ የንፁህ መጠጥ ውኃ፣ የሳኒቴሽን እና የንፅህና አጠባበቅ ለሁሉም በየትኛውም ቦታ በሚል መሪ ሀሳብ የአምስት ዓመት ስትራቴጂውን ከ2023 እስከ 2028 ለመጨረስ አቅዶ እየሠራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አስፋው ዲጋሞ ዋተር ኤድ ኢትዮጵያ በንፁህ መጠጥ ውኃ ተደራሽነት ላይ ሀገሪቱ የያዘችውን የ10 ዓመት ዕቅድ በማሳት ረገድ የራሱን ድርሻ እየተወጣ ነው ብለዋል፡፡
የንፁህ መጠጥ ውኃን ተደራሽ በማድረግም አሻራውን እያሳረፈ የሚገኝ ድርጅት እንደኾነም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ቤቴል መኮንን
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!