
ባሕር ዳር: መስከረም 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተሞችና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) በባሕርዳር ከተማ የሚገኙ ፋብሪካዎችን ተመልክተዋል፡፡
የኢንዱስትሪና እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኀላፊው እንድሪስ አብዱ፣ የአማራ ክልል ኮምዩንኬሽን ቢሮ ኀላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) እና ሌሎችም የሥራ ኀላፊዎች በምልከታው ላይ ተገኝተዋል። ምልከታው ፋብሪካዎች ያሉበትን የሥራ እንቅስቃሴ ለማወቅና ያሉባቸውን ችግር ለመረዳት ያለመ ነው ተብሏል፡፡
የዓባይ የምግብ ዘይት ፋብሪካ ባለቤት ሻምበል መንገሻ ፋብሪካቸው አንድ ሺህ ለሚደርሱ ሠራተኞች የሥራ እድል የፈጠረ ግዙፍ ፋብሪካ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ ፋብሪካው ሥራ መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡የኢንቨስትመንት ቦታዎችን ከሦስተኛ ወገን በቶሎ አለማላቀቅ እና የኃይል አቅርቦት ችግር እንዳለባቸውም አቶ ሻንበል ተናግረዋል፡፡ ፋብሪካቸው የምግብ ዘይት እና የእንስሳት መኖ እንደሚያምርትም አስታውቀዋል፡፡
አለባቸውና እና ማስታዋል የኅብረት ሥራ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ይርጋ አይቸው ድርጅታቸው ጨርቃጨርቅ ላይ መሰረት አድርጎ እየሠራ መኾኑን ተናግረዋል፡፡ በኃይል አቅርቦት ችግር ምክንያት በሙሉ አቅማቸው እያመረቱ አለመኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ የኃይል አቅርቦት ችግሩ እንዲስተካከልላቸውም ጠይቀዋል፡፡ በሰው ኃይል እና በማሽን በኩል ችግር እንዳልገጠማቸው አመላክተዋል፡፡
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባበሪ እና የከተሞችና መሠረተ ልማት ቢሮ ኀላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) ባሕርዳር ከተማ የእድገት ማዕከል መኾኗን ተናግረዋል፡፡ የእድገት ማዕከላት የኾኑ ከተሞችን አቀናጅቶ መሥራት እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡ የተመለከቷቸው ኢንዱስትሪዎች ለሀገር ፍጆታ እና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን እያመረቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ የኢንዱስትሪዎች እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ መኾኑንም አመላክተዋል፡፡
ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ የማቅረብ አቅም ያላቸው ትልልቅ ኢንዱስትሪዎች ለሀገር እድገት መሠረት መኾናቸውንም ገልጸዋል፡፡ የከተሞች እና የኢንዱስትሪ ማዕከላት ፍኖተ ካርታ የተናበበ እንዳልነበር ዶክተር አሕመዲን አንስተዋል። የከተማና የኢንዱስትሪ ማዕከላትን ፍኖተ ካርታ ትስስር በአስር ዓመት እቅዶች ተካትቶ ወደ ሥራ መገባቱንም ተናግረዋል፡፡
ከኃይል አቅርቦት ጋር ያለውን ችግር በሂደት መፍታት ይገባል ነው ያሉት፡፡ በቅርቡ የሚፈቱ የኃይል አቅርቦት ችግሮች መኖራቸውንም ተናግረዋል፡፡ ከተሞችን፣ ኢንዱስትሪዎችን እና አጠቃላይ የልማት ማዕከላትን ኅበረተሰቡን ተሳታፊ በማድረግ የማስተሳሰር ሥራ እንተገብራለንም ብለዋል፡፡
አዲስ የተደራጀው አመራር በርካታ ችግሮችን እየፈታ መኾኑን የተናገሩት ዶክተር አሕመዲን በተለይም በኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለውን ችግር ፈጣን ውሳኔዎች እየወሰነ እየፈታ ይገኛል ነው ያሉት። ችግሮችን ለመፍታት በሚሠሩ ሥራዎች የኅብረሰተቡን ተሳትፎ እና ትስስር እንደሚጠይቁም ገልጸዋል፡፡
ዶክተር አሕመዲን ሰላምን ለማረጋገጥ የኢንዱስትሪ ባለቤቶች እና ሠራተኞች ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡ በባሕርዳር ከተማ ሰላማዊ እንቅስቃሴ በመኖሩ ኢንዱስትሪዎች መደበኛ ሥራቸውን እያከናወኑ እንደሚገኙም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!