
ባሕር ዳር: መስከረም 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ)ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የወረቀትና ወረቀት ፓኬጂንግ ኢንዱስትሪዎች እያጋጠሟቸው ባሉ ችግሮች ዙሪያ የምክክር መድረክ አዘጋጅቷል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል እንደሀገር ካለን አቅም አንፃር የወረቀትና ወረቀት ነክ ተረፈ ምርቶችን በመጠቀም በርካታ የሥራ ዕድል መፍጠር እንችላለን ብለዋል። የፐልፕና ወረቀት ፋብሪካዎች እንደሀገር አቅማቸው እየተጠናከረ ያሉ ኢንዱስትሪዎች መኾናቸውንም ሚኒስትሩ ተናግረዋል። በቁጥር 27 የሚደርሱ ኢንዱስትሪዎች በሀገር ውስጥ ባለሃብቶች ተገንብተው እየሠሩ ሥለመኾኑም ገልጸዋል።
እነዚህ ኢንዱስትሪዎች ከውጭ የሚመጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ረገድ ትልቅ መሻሻል እያሳዩ ስለመኾኑም ጠቁመዋል። በሀገር ውስጥ የሚመረቱት ምርቶች ከ77 በመቶ በላይ ያለውን የሀገር ውስጥ ፍላጎት እንደሸፈኑም ተናግረዋል።
የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም የበለጠ ካሳደግን ከሀገር ውስጥ ፍጆታ አልፈን ለውጭ ገበያ የምናቀርብበት እድል ይኖራል ብለዋል። ይህንን ለማሳካትም የወረቀትና ወረቀት ፓኬጂንግ ሥራን በጥራትና በብዛት ማምረት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ሚኒስትሩ ዘርፉ ከፋብሪካው ጀምሮ ጥሬ እቃው እስከሚገኝበት ቀበሌ ድረስ በርካታ የሥራ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል። ወረቀትና ወረቀት ነክ ተረፈ ምርቶችን በመጠቀም ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠር እንችላለንም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከ30 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿ በትምህርት ላይ የሚገኙባት ሀገር ናት ያሉት ሚኒስትሩ ወረቀት እና የወረቀት ምርቶችን የማቅረብ ጉዳይ ትልቅ ትኩረት የሚሻ መኾኑን ጠቁመዋል።
የወረቀት ተረፈ ምርቶችን መልሶ የመጠቀም አቅም እንደሀገር ሲለካ ከ5 በመቶ አይበልጥም ያሉት ሚኒስትሩ የበለጠ ማደግና መጠናከር እንዳለበትም አሳስበዋል።
የውጭ ምናዛሬ እጥረት፣ የመብራት መቆራረጥ፣ የጉምሩክ አሠራር ቀልጣፋ አለመኾን እና ከውጭ በሚገቡ ያለቀላቸው ምርቶች ላይና ግብዓቱን በሚያስመጡ ያልተመጣጠነ ታክስ መጣሉ ዘርፉን እየፈተኑ ያሉ ተግዳሮቶች ናቸው ተብሏል።
ዘጋቢ:- ድልነሳ መንግሥቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!