
ፀሀይዋ ደመናውን በግማሽ ገርስሳ ጮራዋን ፈንጥቃ በቤቴ መስታወት ላይ አንፀባርቃለች፡፡
ከእንቅልፌ ስነቃ የፀሀይዋን ድምቀት በማየት የረፈደ መስሎኝ በፍጥነት ተነሳሁ፡፡ ሰአቴን ስመለከት ከጠዋቱ 1፡00 ሆኗል፡፡ ወደ ቤተክርስቲያን ለመሄድ በፍጥነት ለባበስኩና ወደ ፈለገ ገነት ቅዱስ ጊዮርጊስ ካቴድራል አመራሁ፡፡ በስተጀርባ በኩል የአብነት ተማሪዎች ዜማ ይሰማል፤ የድምፃቸው ስርቅርቅነት ልብን ይመስጣል፡፡ ቅዳሴውን በእነርሱ አቅራቢያ ቆሜ አስጨረስኩ፡፡ ሰላምታ ተለዋወጥንና ዜማችሁ ደስ ብሎኝ ከእናንተ ጋር መጫወት ፈልጌ መጣሁ አልኳቸው፡፡ “ጥሩ ነው እንጅ!” አለኝ እሱ እያዜመ እነርሱ ሲቀበሉት ሲያስተምር የቆየው ተማሪ፡፡
ጠጋ ብዬ ስለ አብነት ትምህርቱ እና ስለ ሕይወት ልምዱ እንዲያጨውተኝ አስፈቀድኩት፡፡ በሙሉ ፈቃደኝነት፣ በረጋ ንግግር፣ በትህትና ያወራኝ ጀመር፡፡ ‹‹ገና ክፉና ደጉን፣ ጥቅምና ጉዳቱን ሳልለይ በአስራ አንድ አመቴ ነበር ወደ አብነት ትምህርት ቤት የገባሁት፡፡ በመንደራችን ያሉ አንድ መሪጌታ እያየሁ ነበር ወደ ትምህርት ቤቱ መሄድ የጀመርኩት፡፡ ከአካባቢዬ ፎገራ ወረዳ ቋራ አቦ ቤተክርስቲያን ጀምሬ ወደ ጉራአምባ ኪዳነ ምህረት ተዛውሬ ጥቂት ዓመታት ቆይቸ አገሬን ለቀቅኩ፡፡ ወደ ይልማና ዴንሳ ወረዳ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያንም ሄጄ አገልግያለሁ፤ አሁን የ28 ዓመት ወጣት ነኝ፤ በዚህ ትምህርትም 17 ዓመታትን አሳልፌያለሁ›› አለኝ ከልጅነት ትውስታዎቹ በመነሳት ሲያጫውተኝ፡፡
የአብነት ትምህርትን ‹ሀ ግዕዝ› ብሎ ጀምሮ የአቋቋም ትምህርቱንም አጠናቅቋል፡፡ ከዚህ ደረጃ ሲደረስ ልክ እንደ መደበኛ ትምህርት ሁሉ በአብነትም የትምህርት ዘርፍ ይመርጣሉ፡፡ የቅዳሴ ማኅተም፣ የአቋቋም ማኅተም፣ የመጽሐፍ እና የዝማሬ ማኅተም የሚባሉ የትምህርት ዘርፎች እንዳሉ ኤርሚያስ ነግሮኛል፡፡ ‹‹የእኔ ምርጫ የቅዳሴ ማኅተም ስለሆነ በዚህ የትምህርት ዘርፍ ቅኔን፣ አቋቋምን እና ቅዳሴን ጨርሸ መሪጌታነትን እያገባደድኩ ነው፡፡ ይህንኑ ነው የማስተምረው፡፡ ትምህርቱን ሳጠናቅቅ ደግሞ በአብያተ ክርስቲያናት ተቀጥሬ ለማገልገል ነው የምማረው›› ሲል የወደፊት ህልሙን ጭምር አጫወተኝ፡፡ በሃገራችን የትምህርት ታሪክ ተማሪነትን በሁለት ጎራ ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ በአብነት እና በአስኳላ (ዘመናዊ)፡፡ ሁለቱም ዓላማቸው እውቀትን ለመሸመት፤ ጥበብን ለመመርመር፣ ድንቁርናን ለማሸነፍ የሚደረግ ውጣ ውረድ ነው፡፡ የትምህርት አሰጣጥ፣ አቀባበል እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸው ግን ለየቅል ነው፡፡ የቆሎ ተማሪው እየበላ፣ እየለበሰ፣ እያየ፣ ባደገበት ሁኔታ ላይ መሠረቱን ያደርጋል፡፡ አኮፋዳውን ይዞ ከጎጆው ወጥቶ እስኪመለስ ድረስም በክንፍ የሚበሩትን፣ በደረታቸው የሚሳቡትን ፍጥረታት ሁሉ ይቃኛል፡፡ ሊፋለሙት በቁጣ ገስግሰው ወደሱ የሚመጡትን የውሾችን ኃይል እየጣሰ ከማያውቀው መንደር ይገባል፡፡ የሚሰጡትን ቁራሽም ሆነ ጥራጥሬ ሲቀበል የሰዎቹን ርህራሄ ይመለከታል፡፡
ምግብ ብቻ ሳይሆን ለቅኔው የሚሆነውን ሃሳብ ከሕዝብ ይሰበስባል፡፡ ይህንን እያሰበ ሲጓዝ፣ ለሚመለከተው ሁሉ በትካዜ የተዋጠ ይመስላል፤ግን አይደለም፤ ቀለም ገብቶት፤ እውቀትንና እውነትን እየመረመረ እንጂ፡፡ የቆሎ ተማሪ የሚማረውን ትምህርት በቃል የሚማር እንደመሆኑ መጠን ነገ አጠናለሁ፤ በኋላ አነባለሁ ብሎ ጊዜ አይሰጥም፤ ሁል ጊዜ ትምህርት ላይ ነው፤ ሲጓዝም፣ ከጓደኞቹ ጋር ሲነጋገርም ዓላማው ትምህርቱን በቃል መያዝ፤ መመራመር ነው፡፡
ካነጋገርኳቸው ሌሎች የቆሎ ተማሪዎች መካከል ተማሪ ዘላለም ፍሬው ‹‹የቆሎ ተማሪዎች ምግብ የምናገኘው ‹በይንተ ስሟ ለማርያም› ብለን ነው›› ይላል፡፡ የተገኘውን ቁራሽ በፀሃይ አድርቀው አኮችረው እንደሚመገቡም ተናግሯል፡፡ ሊጠይቃቸው የሚሄድ እንግዳም ሲኖር ተቀብለው፣ እግር አጥበው፣ ከሚበሉት አብልተው፣ አሳድረው ይሸኙታል፡፡ የትምህርት አቀባበላቸው እንደየ ትጋታቸው ነው፡፡ ትጉህ ተማሪ አንዴ እንደተነገረው ትምህርቱን ይይዛል፤ ጀማሪ ከሆነ ደግሞ ያስደግማል፤ በማግስቱ ግን ይለምደዋል፡፡
በኢትዮጵያ ደራሲያን ማኅበር የባሕር ዳር ቅርንጫፍ ኘሬዝዳንት ሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን እንዳሉት አሁን የአብነት ተማሪ እየተባለ የሚጠራው ዘመናዊው ትምህርት ባልተስፋፋበት ወቅት ‘ተማሪ’ የሚል ስያሜ ነበረው፡፡ ይህም ስያሜ የተሰጠው እንደ አጫዋች፣ የሚቀኝ እና ብልህ አይነት ሰው ይወሰድ ስለነበር ነው፡፡ ከዚህም በመነሳት ‘የተማሪን ብልሃት አይጥ አይበጥሰውም’ የሚባል አባባል አለ፡፡
በመሆኑም የአብነት ተማሪ፣ የአብነት ትምህርት ቤት እና የአብነት መምህር በሚል እንደሚጠራ ሊቀ ኅሩያን በላይ መኮንን አብራርተዋል፡፡ ሊቀ ህሩያን እንደሚሉት ትምህርቱ ከክርስትና ኃይማኖት ጋር የተገናኘ ነው፡፡ እምነትና ስነ ምግባር ደግሞ ነብስና ሥጋ ማለት ናቸው፡፡ እምነት ደግሞ በበጐ ስራ ካልተገለፀ ዋጋ ስለሌለው የአብነት ትምህርት መሠረቱ የኃይማኖት ትምህርት ነው፡፡ ‹‹ኃይማኖቱ ደግሞ በፍፁም ልቦናው መቀበል ፍቅርን፣ ትህትናን ሰው ማክበርን ያስተምራል›› ብለዋል ሊቀ ኅሩያን፡፡ ይህንንም ከእናት አባት፣ መምህሩን እና ሌሎችንም ሰዎች ከማክበር ይጀምራል፡፡
ትምህርት ቤቱ በታዛዠነት መምህሩ ሲመጣ ከተቀመጠበት ተነስቶ፣ እግርን አጥቦ ስሞ፣ መቋሚያን ተቀብሎ፣ ተላልኮ ትህትናንና ፍቅርን በመማር ታርሞና ተስተካክሎ የሚያድግበት ነው፡፡ እንደ ሊቀ ኅሩያን ማብራሪያ የአብነት ትምህርት ለዘመናዊ ትምህርትም መሠረቱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፊደልን፣ የቁጥር ቀመርን፣ ስነ ጽሕፈትና ስነ ጽሑፍን የተወረሰው ከአብነት ትምህርት ነው፡፡ ቀደም ባሉት መንግስታት የአስኳላ ትምህርትን ለመመስረትም ሆነ በመንግሥት ተቋማት ለማገልገል ሲፈለግ ግለሰቦች የተወሰዱት ከአብነት ትምህርት ሊሂቃን ነበር፡፡ ለዚህም እንደ ምሳሌ እነ ሀዲስ አለማየሁና ዮፍታሄ ንጉሴ ይጠቀሳሉ፡፡
በአስኳላ ትምህርት ቤቶችም እስከ ደርግ መንግስት ድረስ የስነ-ምግባር ትምህርት እየተባለም እንደ አንድ የትምህርት አይነት ሊሂቃኑ ያስተምሩ ነበር፡፡ በጨቅላነት ዕድሜ በቆሎ ትምህርት ቤት ፊደል የቆጠረ ሰው ወደ መደበኛ ትምህርት ቤት ሲገባ በስነ ምግባርም ሆነ በትምህርት አቀባበል ደረጃው የተሻለ ሲሆን ይስተዋላል፡፡ ‹‹ትውልዱ ሃገር በማልማትና በመገንባት ሂደት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ስነ-ምግባርን ከሃይማኖት ተቋማት፣ መደበኛ ትምህርትን ከአዳዲስ አሰራሮችና ቴክኖሎጅዎች ጋር በማስተሳሰር ተማሪዎችን ማብቃት ይገባል የሚል ምክር አላቸው ሊቀ ኅሩያን፡፡
ዘጋቢ፡- ዘመንሽ አዱኛው