
አዲስ አበባ፡ መስከረም 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር 26 ሀገራት የሚሳተፉበትን የእንቆጳ ጉባዔ ከጥቅምት 1 እስከ 2/2016 ዓ.ም እንደሚያዘጋጅ አስታውቋል።
የኢፌዴሪ ሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ትኩረቱን በኢንተርፕርነርሺፕ፣ ቴክኖሎጂ እና ሥራ ፈጠራ ላይ ያደረገ ጉባዔ በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚያካሂድ ነው የተገለጸው።
ጉባዔውን በተመለከተ መግለጫ የሰጡት የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን ጉባዔው የተዘጋጀው የሥራ ፈጠራን በማጎልበት ኢትዮጵያ ያላትን ጸጋዎች እና ሃብቶችን ለማስተዋወቅ እንደኾነ አብራርተዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው በኢንተርፕርነሮች፣ በኢኖቬተሮች፣ በቴክኖሎጅ አልሚዎች፣ በፖሊሲ አውጭዎች እና በጀማሪ የንግድ ባለሙያዎች የትምህርት ተቋማትን በአንድ መድረክ በማገናኘት በኢትዮጵያ የኢንተርፕነርሽፕ ባሕልን ለማሳደግ ዓላማ አድርጎ የተዘጋጀ ጉባኤ መኾኑን ገልጸዋል።
በጉባዔው የመንግሥት እና የግል ድርጅቶች ይሳተፋሉ ተቦሏል፡፡ አቶ ንጉሱ በጉባዔው ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት የፓናል ውይይቶች እንደሚካሄድም ጠቅሰዋል፡፡
የተለያዩ አካላትን የማስተሳሰር ሥራዎች እና በሥራ ፈጠራ የተሠሩ ፈጠራዎች የሚታዩበት ኤግዚቢሽን በሚሊኒየም አዳራሽ እንደሚኖርም ተገልጿል።
ጉባዔው የሥራ ፈጠራ እና ኢንተርፕርነርሽፕ እንዲያድግ አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሏል፡፡
በጉባዔው ከ30 በመቶ በላይ የሚኾኑት ተሳታፊዎች የውጭ ሀገራት ዜጎች መኾናቸውም ተገልጿል።
ዘጋቢ፡- ራሄል ደምሰው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!