
ባሕር ዳር: መስከረም 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) በወቅታዊ የክልሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከአሚኮ ጋር ቆይታ የነበራቸው የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የአማራ ሕዝብ የቆዩ እና ተለይተው ያደሩ ግልጽ ጥያቄዎች አሉት ብለዋል። “የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄዎች ናቸው” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የክልሉ ሕዝብ ጥያቄዎች የሚፈቱትም በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ነው ብለዋል።
የራሱን አሳልፎ መስጠት የማይፈልገው የአማራ ሕዝብ የሌሎችንም አልፎ አይነካምም፤ አይጠይቅምም ነው ያሉት። የሕዝቡ ጥያቄዎች ለሀገራዊ ለውጡ ገፊ ምክንያቶች ናቸው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ጥያቄዎቹ ግልጽ፣ ተለይተው ያደሩ እና ልዩነት የማይስተዋልባቸው ናቸው ብለዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ የሕዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ በክልሉም ሆነ በፌደራል መንግሥቱ ዘንድ ልዩነት የለም ነው ያሉት። ጥያቄዎቹ በሚፈቱበት መንገድ ዙሪያ እንኳን በመንግሥታቸውም ሆነ በፓርቲያቸው ዘንድ ልዩነት እንደሌለ አንስተዋል።
የአማራ ሕዝብ ጥያቄዎች በረጅም ሀገረ መንግሥታዊ ሂደት ውስጥ ፖለቲካዊ ልዩነቶች የፈጠሯቸው ክፍተቶች ናቸው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ አንዳንዶቹን ችግሮች ለመፍታት ጊዜ እና ኢትዮጵያዊ ትብብርን የሚጠይቁ ናቸውም ብለዋል።
የአማራ ሕዝብ ሕብረ ብሔራዊነቷ የጸና እና የተጠበቀ ሀገር መገንባት ይፈልጋል፤ ነገር ግን የሕዝቡን የላቀ ሀገረ መንግሥታዊ ሥነ ልቦና ስሪት በሚሸረሽር መንገድ የተፈጠሩት የዘመናት ችግሮች የሚፈቱት የሕዝቡን ማኅበረሰባዊ ልዕልና በጠበቀ መንገድ ፍጹም ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ኾኖ ነው ብለዋል። ለዚህም ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድም ሕዝቦች ጋር ያለውን ግንኙነት ጤናማ እና በትብብር ላይ የተመሰረተ ለማድረግ እየተሠራ እንደሆነ አንስተዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ እየተፈቱ ያሉ ጥያቄዎችን ለሕዝብ በማሳወቅ እና በመግለጽ በኩል ውስንነቶች ነበሩብን ብለዋል። አንዳንዶቹ የሕዝብ ዋና ዋና ጥያቄዎች ምላሽ አግኝተዋል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ሕጋዊ መልክ ማስያዝ እና ማጽናትን ግን ይጠይቃል ነው ያሉት። ሕዝቡ በተለመደው አስተዋይነት እና አርቆ አሳቢነት የተገኙትን መልካም ድሎች እና እድሎች አጽንቶ መጠበቅ እንዳለበት በማሳሰብ።
የአማራን ሕዝብ ተለይተው ያደሩ እና በመመለስ ላይ ያሉ ጥያቄዎችን እንደ አዲስ መዝዞ ሕዝብን ለትርምስ መጋበዝ ግን ደግሞ እና ደጋግሞ ማሰብን የሚጠይቅ የተሳሳተ መንገድ ነው ብለዋል። በክልሉ ውስጥ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የክልሉን መንግሥት እና ሕዝብ አቅም ያሳጣል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ለክልሉ ሕዝብ የሚቆረቆር ሁሉ እጆቹን ከእንደዚህ አይነት አካሄዶች ማንሳት አለበት ነው ያሉት።
የክልሉን ሕዝብ እና መንግሥት የመደራደር፣ የመከራከር እና የመመካከር አቅም ከሚፈትኑ ግጭቶች መውጣት እና ሰላማዊ አማራጮችን መመልከት ተገቢ ነው ብለዋል። በክልሉ ሕዝብ ጉዳይ የማያገባው እና አብዝቶ የሚያገባው የለም፤ አንዱን ተቆርቋሪ ሌላውን የማይቆረቆር አድርጎ ማቅረብ ጊዜው ያለፈበት የፖለቲካ ሸፍጥ ነውም ብለውታል። ከምንም በላይ አንድነትን ማጠናከር እና በጋራ መቆም እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
በክልሉ በተፈጠረው ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ውስጥ የተለየ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች አሉ ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ አብዛኞቹ ወደ ግጭቱ የገቡት ግን አንድም ተገድደው አንዳንዶቹም በብዥታ ነው ብለዋል።
ባለማስተዋል እና በብዥታ ተገቢ ያልሆነውን መንገድ የተከተሉ ሁሉ ወደ ሰላማዊ አማራጮች እንዲመለሱም ጠይቀዋል። በቀጣይ በሚፈጠሩ ሕዝባዊ ውይይቶች የሕዝብ ጥያቄዎች ያሉበትን አሁናዊ ሁኔታ በየደረጃው ለሕዝብ ግልጽ ይደረጋሉ ብለዋል። የክልሉን ሕዝብ ሚዛናዊ እና ፍትሃዊ ጥያቄዎች ለመመለስ የሚደረገው ጥረት ግን አሁንም በተጠና እና በተጠናከረ መንገድ ይቀጥላል ብለዋል።
ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!