
ሁመራ፡ መስከረም 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በዓለም ለ33ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ32ኛ ጊዜ የሚከበረው የአረጋውያን ቀን በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ለ2ኛ ጊዜ በሁመራ ከተማ ተከብሯል።
“የአረጋዊያን መብት ማክበር ትውልድን ለማሻገር ” በሚል መሪ ቃል በተካሄደው መርሐ ግብር የዞኑ እና የወረዳ የሥራ ኀላፊዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው አረጋውያን ተሳትፈዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ አረጋዊያን ልጆቻችን ስለ ሀገር ፍቅር እንዲሁም ስለ ባሕልና እሴቶቻችን በማስተማር ቀጣዩ ትውልድ ሀገርን ከነክብሯ እንዲጠብቅ የበኩላችንን ኀላፊነት ልንወጣ ይገባል ብለዋል።
የመርሐ ግብሩ መካሄድ አረጋውያን ለሀገር የከፈሉትን መስዋዕት የሚዘክር መኾኑም ተነስቷል። አረጋውያኑ ለአሁኑ ትውልድ ከጦርነት ይልቅ ውይይትን፣ ከጠብ ይልቅ ፍቅርን፣ ከመለያየት ይልቅ አንድነትን ማስተማር አለብን ነው ያሉት።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ዞን ሴቶች ህጻናትና ማኅበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ወይዘሮ ማህደር አድማሴ አረጋውያን በላብና ደማቸው የጸናች ሀገርን ለትውልዱ አስረክበዋል ብለዋል። የአረጋዊያንን መብት በማክበር ልናግዛቸውና ልንደግፋቸው ይገባል ሲሉም መልእክት አስተላልፈዋል።
የሀገርን ጥቅም በማስቀደም ለሀገር ክብር የተዋደቁ አረጋውያን ስማቸው በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በክብር ተቀምጦ ይገኛል ሲሉም ገልጸዋል። የአሁኑ ትውልድ ወጣቶች አረጋውያን ለሀገራቸው የከፈሉትን መስዋዕትነት በማሰብ ሊንከባከባቸው እንደሚገባም አሳስበዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!