“በአዲስ የተደራጀው አመራር የክልሉን ወቅታዊ ችግር ለመፍታት እየሠራ ነው” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

76

ባሕር ዳር: መስከረም 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ካለፈው ሐምሌ ወር መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ በክልሉ በርካታ አካባቢዎች መጠነ ሰፊ የጸጥታ ችግር ተፈጥሮ እንደነበር ይታወሳል። ችግሩን ተከትሎ ጥልቅ ግምገማ ያደረገው የክልሉ መንግሥት ከክልል እስከ ቀበሌ የሚደርስ የአመራር መልሶ ማደራጀት እና ምደባ ሠርቷል።

በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ዘርፈ ብዙ ምክንያቶች እንደነበሩበትም በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ገልጸዋል። የክልሉ መንግሥት በችግርም ውስጥ ኾኖ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ዙሪያ ጥልቅ ግምገማ አድርጓል ብለዋል።

ርእሰ መሥተዳድሩ የክልሉ መንግሥት የገጠመውን ወቅታዊ የጸጥታ ችግር ብቻ ሳይሆን የመውጫ መንገዶቹም ላይ ጊዜ ወስዶ በጥልቀት መክሯልም ነው ያሉት። የክልሉ መንግሥት ለተፈጠሩት ወቅታዊ ችግሮች መውጫ ያላቸውን የመፍትሄ መንገዶች መሸከም የሚችል አመራር መልሶ መደራጀት እና ምደባ ማድረጉንም አንስተዋል።

የአመራር ምደባው እና መልሶ የማደራጀት ሂደቱ ሁለት የተለያዩ ግን ደግሞ ተመጋጋቢ ገጾች አሉት ያሉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ የመጀመሪያው ከክልል እስከ ቀበሌ የሚደርሰው የፖለቲካ አመራር አደረጃጀት እና ምደባ ነው ብለዋል።

በሁለተኛ ደረጃ መልሶ ማደራጀት የተሰራው በየደረጃው የሚገኘው የክልሉ መንግሥት የጸጥታ መዋቅር ነው። አደረጃጀቱ የክልሉን ሰላምና ደኅንነት፣ ፖሊስ፣ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር እና ሚሊሻን የሚያካትት እንደሆነም አንስተዋል።

ከክልል እስከ ቀበሌ የተንሰላሰለው የፖለቲካ አመራሩ መልሶ ማደራጀት ሂደት በበርካታ አካባቢዎች እስከ ወረዳ ድረስ ተጠናቅቋል ነው ያሉት። በቀጣይም ሕዝብን ባሳተፈ መንገድ በቀበሌ ደረጃ የፖለቲካ አመራሩን መልሶ የማደራጀት ሥራው ይቀጥላል ብለዋል ርእሰ መሥተዳድሩ።

ሌላው በክልሉ መልሶ የማደራጀት እና ምደባ የተሠራው በክልሉ የጸጥታ መዋቅር ውስጥ ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ይህም እስከ ወረዳ ድረስ በአብዛኛው የክልሉ አካባቢዎች ተጠናቋል ብለዋል። በቀበሌ ደረጃ የሚካሄደው የጸጥታ መዋቅር በተለይም ደግሞ ሚሊሻን መልሶ የማደራጀቱ ሂደት ሕዝቡን ባሳተፈ መልኩ በቀጣይ ቅርብ ጊዜያት ይሠራል ብለዋል።

በክልሉ ከተፈጠረው የጸጥታ ችግር ማግስት መልሶ የተደራጀው የፖለቲካ እና የጸጥታ አመራር ከመደበኛ ሥራዎቹ ጎን ለጎን በየደረጃው ሥልጠና እና ውይይት እያደረገ ነው ተብሏል። ሥልጠና እና ውይይቱ ክልሉ ከገጠመው ችግር ለመውጣት የጋራ የሆነ ሕጋዊና ፖለቲካዊ ቅርጽ እና አቋም ለማስያዝ ያለመ ነው ተብሏል።

“ሁሌም መሪ የሚፈጠረው በምቹ ሁኔታ ውስጥ አይደለም” ያሉት ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ወደ ኅላፊነት የመጡ አመራሮች በአዲስ ስሜት እና መንፈስ ክልሉን ወደ ነበረበት ለመመለስ እየሠሩ ነው ብለዋል።

ርእሰ መሥተዳድሩ በየደረጃው የሚገኘውን የክልሉን መንግሥት አመራር መልሶ ማደራጀት ያስፈለገው ክልሉ የገጠመውን የጸጥታ እና የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታት እንደሆነ ገልጸዋል። ያደሩ እና ሥር የሰደዱ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የአመራር ቁመና ለመፍጠር የተደረገው ጥረት ከሞላ ጎደል ስኬታማ እንደሆነም አንስተዋል።

የአመራር መልሶ ማደራጀት ሥራው ዓላማው ግለሰቦችን መቀያየር ብቻ አይደለም ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ምደባው የአመራር መመዘኛ መስፈርቶቹን መሠረት ያደረገ ነበርም ብለዋል። የፖለቲካ አመራሩንም ሆነ የጸጥታ መዋቅሩን በቅርብ እየተከታተሉ መደገፍ ከሕዝቡ እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleየዓለም ዋንጫ ዳግም በአፍሪካ ምድር ሊካሄድ ነው።
Next articleቀጣዩ ትውልድ ሀገርን ከነክብሯ እንዲጠብቅ የበኩላችንን ኀላፊነት ልንወጣ ይገባል ሲሉ የሁመራ ከተማ አረጋውያን ተናገሩ።