የክልሉ ሰላም እየተሻሻለ መምጣቱን ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አስታወቁ።

52

ባሕር ዳር: መስከረም 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) ካለፈው ሐምሌ ወር መጨረሻ አካባቢ ጀምሮ በክልሉ በርካታ አካባቢዎች የተፈጠረው የሰላም እጦት ዘርፈ ብዙ ጉዳቶችን አስከትሏል። ሰብዓዊ ጉዳትን፣ ምጣኔ ሃብታዊ ድቀትን እና ቁሳዊ ውድመትን ያስከተለው ግጭት የሕዝቡ አስተዋይነት እና የጸጥታ ኃይሉ ትጋት ባይጨመርበት ኖሮ አደጋው የከፍም ሊሆን ይችል እንደነበር ተመላክቷል።

በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከአሚኮ ጋር ቆይታ ያደረጉት የክልሉ ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ግጭቱ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል በቁጥጥር ሥር እየዋለ ነው ብለዋል። በክልሉ በርካታ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ተከትሎ ሕዝቡ የሰላሙ ባለቤት እና ደጋፊ ኾኗል ነው ያሉት።

በክልሉ የተፈጠረው ግጭት በንጹሃን ዜጎች ላይ ጉዳትን እና በክልሉ ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ላይ ችግር አስከትሏል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በክልሉ የጸጥታ መዋቅር እና በሀገር መከላከያ ሠራዊት ብርቱ ጥረት የከፋ ውድመት ሳያስከትል እየተቀለበሰ መምጣቱን ገልጸዋል። በተፈጠረው ግጭት የክልሉ ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ተገትቶ ነበር ብለዋል።

የክልሉ ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል ሲባል የነበረውን የግጭት ድባብ አሁን ካለው አንጻራዊ ሰላም ጋር እያነጻጸሩ ማየት ያስፈልጋልም ነው ያሉት።

ርእሰ መሥተዳድሩ ግጭቱ በክልሉ በርካታ አካባቢዎች ሲፈጠር የሕዝብ እና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ እንደነበር አንስተዋል። አሁን ላይ በክልሉ በርካታ አካባቢዎች ሰላማዊ እንቅስቃሴ መኖሩን አስገንዝበዋል።

ክልሉን የግጭት ማዕከል በማድረግ የማተራመስ የተለየ ፍላጎት የነበራቸው ቡድኖች ህልማቸው እንደማይሳካ አውቀዋል ነው ያሉት። ሕዝቡም በሂደት የሰላሙ ባለቤት እየሆነ መምጣቱን ርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል።

በክልሉ ተፈጥሮ የነበረው ግጭት በትምህርት፣ በጤና እና በግብርና ሥራዎች ላይ የፈጠረው አሉታዊ ተፅእኖ ከባድ ነበር ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ አዝማሚያው የአማራን ሕዝብ መሠረታዊ ፍላጎት እና እውነት ከግምት ያስገባ አልነበረም ብለዋል።

ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ግጭቱ መደበኛ የሆነውን የንግድ ሥርዓት አስተጓጉሏል፣ የመማር ማስተማሩን በርሐ ግብር አጓቷል፣ ከምንም በላይ በሕዝቡ ወጥቶ መግባት ላይ የስጋት ደመና አጥልቷል ነው ያሉት።

አሁን ላይ በክልሉ የሚገኙ ዋና ዋና ከተሞችን ጨምሮ በክልሉ በርካታ አካባቢዎች አንጻራዊ ሰላም ሰፍኗል ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የተገኘው የሰላም አየር በክልሉ የጸጥታ መዋቅር እና በሀገር መከላከያ ሠራዊት ቅንጅታዊ መስዋእትነት የተገኘ ነው ብለዋል። የክልሉ ሕዝብ እና መንግሥት ለክልሉ ሰላም ዋጋ የከፈሉትን ሁሉ ያመሰግናልም ብለዋል።

በቀጣይም በክልሉ ውስን አካባቢዎች የሚስተዋለውን ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ ወደ ሕጋዊ መስመር ለማምጣት ሕግ የማስከበሩ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ። ሕዝቡ ዘላቂ ሰላም እስኪሰፍን ከጸጥታ ኃይሉ ጋር የሚያደርገውን ቀና ትብብርም አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

የተለየ ሃሳብ እና ሰላማዊ የሆነ አማራጭ ያለው ሁሉ ሃሳቡን እና አመለካከቱን የሚያራምድበት ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ መንገዶች ዝግ አለመሆናቸውንም አንስተዋል። ሕጋዊ የሆነ የመንግሥትን ሥልጣን በኃይል ለመቆጣጠር ማሰብ ግን ሕዝብን ለስቃይ እና ክልሉን ወደ ኋላ ከመመለስ ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው መረዳት ይገባል ነው ያሉት።

የክልሉ ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቷል፤ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ ግን አሁንም ቀሪ ሥራዎች መኖራቸውን ርእሰ መሥተዳድሩ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፦ ታዘብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“ፈጣን ውሳኔዎችን በመወሰን በኢንዱስተሪዎች ላይ የሚታየውን ችግር እየፈታን ነው” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)
Next articleየዓለም ዋንጫ ዳግም በአፍሪካ ምድር ሊካሄድ ነው።