
ባሕር ዳር: መስከረም 24/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በምክትል ርእሰ መሥተዳደር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪ እና የከተሞችና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) በባሕር ዳር ከተማ የተለያዩ ፋብሪካዎችን ተመልክተዋል።
በጉብኝቱ በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የከተማ ዘርፍ አስተባባሪና የከተሞችና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር) ጨምሮ የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ እንድሪስ አብዱ፣ የአማራ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ መንገሻ ፈንታው (ዶ.ር) ተገኝተዋል።
ዶክተር አሕመዲን ባሕር ዳር ከተማ ውስጥ ያሉ ኢንዱስትሪዎች የሀገራዊ እድገት መሠረት መኾናቸውን ተናግረዋል። በምልከታቸውም ለሀገር ውስጥ ፍጆታ እና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ተስፋ ሰጪ ጅምሮችን ማየታቸውን ተናግረዋል።
የልማት ትስስሮችን በማጠናከር የከተማውን እድገት ከኢንዱስትሪዎች መሠረተ ልማት ጋር የማዋሃድ ሥራ ይሠራል ነው ያሉት። በኢንዱስትሪዎች ላይ የሚስተዋለውን የኃይል አቅርቦት ችግርን እንፈታለንም ብለዋል።
ፈጣን ውሳኔዎችን እየወሰኑ በኢንዱስተሪዎች ላይ እየታየ ያለው ችግር እየፈቱ መኾናቸውንም አስታውቀዋል። ሰላምን በማረጋገጥ ኢንዱስትሪዎችን በሙሉ አቅሙ ማሠራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!