“430 ሚሊዮን ብር ተመድቦ የድጋፍ እህል ለመግዛት ተወስኗል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ

49

ባሕር ዳር: መስከረም 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) መንግሥት 430 ሚሊዮን ብር መድቦ በዝናብ እጥረት ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን ለመደገፍ የሚውል የእርዳታ እህል ለመግዛት መወሰኑን የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ አስታውቀዋል። ርእሰ መሥተዳድሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ በክልሉ 8 ዞኖች እና 39 ቀበሌዎች የዝናብ እጥረት በመከሰቱ ነዋሪዎች ተቸግረዋል ብለዋል። “ሕዝባችን ሲቸገር ቀድመን መድረስ አለብን”

ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ የዝናብ እጥረት ያጋጠማቸውን አካባቢዎች ተዘዋውሮ በመመልከት የሕዝቡን ችግር ለይቶ ማወቅ መቻሉን ገልጸዋል።

ለችግር የተጋለጡ ወገኖች ፈጣን ድጋፍ እንዲያገኙ ቡድን ተቋቁሞ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መገባቱን ነው ያስረዱት። በእጃችን ላይ ያለውን ሃብት በመጠቀም የቅድሚያ ቅድሚያ ለሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች ድጋፍ መላክ ተችሏልም ብለዋል።

“ችግሩ መጠነ ሰፊ ነው” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በክልሉ ያለው ለድጋፍ የሚውል ሃብት ውስን ቢኾንም ሌሎች አማራጮችን በሙሉ አሟጦ በመጠቀም ዜጎችን ከችግር ለማውጣት እንጥራለን ብለዋል።

የተወሰነው የ430 ሚሊዮን ብር የድጋፍ እህል ግዥም ቢኾን በቂ አይደለም ነው ያሉት። የክልሉ መንግሥት የችግሩን መጠን በመለየት ተጨማሪ ረጅ ድርጅቶችን የማፈላለግ እና የማስተባበር ሥራ ያከናውናል ነው ያሉት።

የተፈጠረው የዝናብ እጥረት አደጋ ከክልሉ ወቅታዊ ኹኔታዎች ጋር ተዳምሮ ተጨማሪ ጫና ቢኾንም መንግሥት ለተቸገሩ ዜጎች ለመድረስ ሁሉንም አይነት ጥረት እያደረገ ነው ብለዋል። የዝናብ እጥረት ያላጋጠማቸው እና ትርፍ አምራች የኾኑ አካባቢዎች ለተቸገሩ ወገኖች ፈጥነው በመድረስ ወገናዊ አለኝታነታቸውን እንዲያረጋግጡም መልእክት አስተላልፈዋል።

ርእሰ መሥተዳድሩ የተከሰተው የሰላም እጦት የድጋፍ እህል ለማጓጓዝ ፈተና መኾኑንም አንስተዋል። የድጋፍ ቁሳቁስ ዝውውሩን ከማስተጓጎል በተጨማሪ የዝርፊያ ሙከራዎች መስተዋላቸውን አብራርተዋል።

“ለሁሉም ነገር መፍትሔ ለመስጠት መሠረቱ ሰላም ነው” ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን ሕይወት ለመታደግ ኀላፊነት የሚሰማው በሙሉ ለአካባቢው ሰላም ዘብ መቆም አለበት ብለዋል።

በዝናብ እጥረት፣ በመፈናቀል እና በልዩ ልዩ ምክንያቶች ለችግር የተጋለጡ ወገኖች ድጋፍ እንዲያገኙ እና በዘላቂነት እንዲቋቋሙ በቁርጠኝነት እንደሚሠራም ርእሰ መሥተዳድሩ አስገንዝበዋል።

ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleወደ መማር ማስተማሩ ያልገቡ ትምህርት ቤቶች ወደ ሥራቸው እንዲገቡ የደቡብ ጎንደር ዞን ትምህር መምሪያ አሳሰበ፡፡
Next article“ፈጣን ውሳኔዎችን በመወሰን በኢንዱስተሪዎች ላይ የሚታየውን ችግር እየፈታን ነው” አሕመዲን ሙሐመድ (ዶ.ር)