
ባሕር ዳር፡- ጥር 22/2012ዓ.ም (አብመድ) የአንበጣ መንጋ ጉዳት እንዳያደርስ ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ የኢፌዴሪ ግብርና ሚኒስቴር ጥሪ አቀረበ፡፡
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ የአንበጣ መንጋው የከፋ ጉዳት ከማድረሱ በፊት ለመከላከል ኅብረተሰቡ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርቧል፡፡ በዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት የአንበጣ መረጃ ክፍል ትንበያ መሠረት የአንበጣ መንጋ የነፋስን አቅጣጫ ተከትሎ ከሳዑዲ አረቢያ ቀይ ባሕርን አቋርጦ በየመን በኩል ባለፈው ሰኔ መጨረሻ አፋር ላይ መከሰቱን አስታውሷል፡፡
በሃገሪቱ የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ በመከላከል ረገድ ከባህላዊ ዘዴ ባሻገር ከእግረኛ እስከ አውሮፕላን በጸረ ተባይ ርጭት የመከላከል ሥራ ሲያከናውን መቆየቱንም ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል፡፡ በዚህም በአፋር፣ በአማራ፣ በትግራይና በሌሎች ክልሎች ተከስቶ የነበረው የአንበጣ መንጋ በሰብል ላይ የጎላ ጉዳት ሳያደርስ መከላከል ተችሏል ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡
በአሁኑ ደግሞ ወቅት የአንባጣው መንጋ ደቡብ ምስራቅና ደቡብ ኦሮሚያ እንዲሁም በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መከሰቱን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡ እንደ ግብርና ሚኒስቴር መግለጫ ተባዩ ጉዳት እንዳያደርስ በአራት አውሮፕላኖች የታገዘ የጸረ ተባይ ርጭት እና በኅብረተሰቡ ተሳትፎ በባህላዊ መንገድ ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡
የአንበጣ መንጋ በቀን ከ150 እስከ 300 ኪሎ ሜትር የሚጓዝና ሁሉንም ሰብሎችና የዕጽዋት አይነቶች የሚበላ እጅግ አደገኛ ነፍሳት ነው፡፡ ስለሆነ ይህን ተባይ በመከላከል ረገድ በሚደረገው ሁለንተናዊ እንቅስቃሴ ሁሉም ሊረባረብ እንደሚገባ ሚኒስቴሩ አሳስቧል፡፡