ወደ መማር ማስተማሩ ያልገቡ ትምህርት ቤቶች ወደ ሥራቸው እንዲገቡ የደቡብ ጎንደር ዞን ትምህር መምሪያ አሳሰበ፡፡

40

ባሕር ዳር: መስከረም 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ክልል ተፈጥሮ በነበረው የሰላም እጦት ምክንያት ትምህርት ቤቶች በተያዘላቸው ጊዜ ወደ ሥራ ሳይገቡ ቆይተዋል፡፡

ይሁን እንጅ ክልሉ በሠራው ሰፊ የሕግ ማስከበር ሥራ አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ወደ ሥራ ተመልሰዋል፡፡

ወደ ሥራ የገቡት ትምህርት ቤቶችም ለትምህርት ዓመቱ የሚያስፈልገውን ዝግጅት በማጠናቀቅ የትምህርት ዓመቱን ጀምረዋል፡፡

በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ግን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እየመጡ አለመኾኑን እና ትምህርት ቤቶችም አለመከፈታቸውን አሚኮ ለማረጋገጥ ችሏል፡፡

በደቡብ ጎንደር ዞን የሚገኙ አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ወደ ሥራ ገበታቸው ይመለሱ እንጂ አሁንም ወደ መማር ማስተማሩ ያልመጡ ትምህርት ቤቶች እና ተማሪዎች መኖራቸው እየተገለጸ ነው፡፡

በደቡብ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ የእቅድ ዝግጅት እና ክትትል ቡድን መሪ ታረቀኝ ጌታነህ እንደነገሩን በዞኑ ካሉ 1ሺህ 80 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ወደ መማር ማስተማሩ የገቡት 695 ትምህርት ቤቶች ናቸው፡፡

ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አኳያ ሲታይ ደግሞ በዞኑ ከሚገኙ 65 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ወደ ሥራ ገብተው ተማሪዎቻቸውን ተቀብለው የዓመቱን ትምህርት ማስተማር የጀመሩት 24 ናቸው ብለዋል፡፡

አቶ ታረቀኝ እንዳሉን ትምህርት በጀመሩ ትምህርት ቤቶችም ተማሪዎች ለምዝገባ ተገኝተው ቢመዘገቡም በሚፈለገው ቁጥር በመማር ማስተማሩ ላይ እየተገኙ አለመኾናቸን ነው ያስገነዘቡት፡፡

በዞኑ ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አኳያ 428 ሺህ 435 ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለመከታተል የተመዘገቡ ቢኾንም አብዛኞቹ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው የማቆራረጥ ኹኔታ እየታየ ስለመኾኑ ነው የተናገሩት፡፡

ከሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አኳያ 75 ሺህ 844 ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለመከታተል ተመዝግበዋል ብለዋል፡፡

ከቅድመ መደበኛ ትምህርት አኳያ 44ሺህ 763 ተማሪዎች ሲመዘገቡ የተግባር ተኮር የጎልማሶች ትምህርታቸውን ለመከታተል 33ሺህ 487 ተማሪች ተመዝግበዋል ነው ያሉት፡፡

እንደ አቶ ታረቀኝ ማብራሪያ ከኾነ በክልሉ በአካባቢው ከሚታየው የሰላም ኹኔታ አኳያ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው መገኘት ላይ መቆራረጥ ይስተዋላል ነው ያሉት፡፡

መቆራረጡ የተከሰተው ካለው የሰላም ኹኔታ አኳያ ወላጆች ካላቸው ስጋት በመነጨ ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዳይሄዱ ስለሚያደርጉ ስለመኾኑ ገልጸው በተቻለ መጠን አሁን ላይ ያለውን የሰላም ኹኔታ በመገንዘብ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

የትምህርት መቆራረጡ በተማሪዎች የትምህርት አቀባበል ላይ ተጽዕኖ ስለሚያስከትል ሁሉም ትኩረት ሰጥቶ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ሊረባረብ ይገባል ነው ያሉት፡፡

በዞኑ ያሉ እና ተማሪዎቻቸውን ያልተቀበሉ ትምህርት ቤቶችም ተከፍተው ወደ መደበኛ የመማር ማስተማር ሥራቸው እንዲመለሱ የሁሉንም እገዛ እንደሚፈልግ አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“የአማራ ክልልን ሕዝብ እወዳለሁ የሚል ሁሉ ለክልሉ ዘላቂ ሰላም ዘብ ይቁም” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ
Next article“430 ሚሊዮን ብር ተመድቦ የድጋፍ እህል ለመግዛት ተወስኗል” ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ