
ባሕር ዳር: መስከረም 24/2015 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ ከአሚኮ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅታዊ የክልሉን ኹኔታ የተመለከቱ ጉዳዮችን አብራርተዋል። ርእሰ መሥተዳድሩ የክልሉን የተሟላ ሰላም በአጭር ጊዜ ውስጥ እና በዘላቂነት በማረጋገጥ ወደ መደበኛ የልማት ሥራዎች በሙሉ ልብ መግባት ያስፈልጋል ብለዋል።
ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በአዳዲስ አመራሮች የተዋቀረው የክልሉ መንግሥት የመልካም አስተዳደር እና የልማት ሥራዎችን በፍጥነት እና በተሟላ ኹኔታ ማከናወን የሚችለው በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች አስተማማኝ ሰላም ሲሰፍን ብቻ ነው ብለዋል።
“የአማራን ሕዝብ ሰላም እና ልማት ከማረጋገጥ የዘለለ ሌላ ተቀዳሚ ዓላማ የለንም” ሲሉም ገልጸዋል። ሕዝቡ ከአመራሩ ጋር በጋራ በመቆም፣ በመደጋገፍ፣ ታሪክና ማንነቱን የሚመጥን የሰከነ ውይይት በማድረግ የተፈጠሩ ችግሮችን በሙሉ መፍታት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ በተለያዩ አደናጋሪ የፖለቲካ እሳቤዎች በመሳሳት ወደ አላስፈላጊ ግጭት የሚገቡ ወንድሞች አርቀው ማሰብ እና ከድርጊታቸው መቆጠብ እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
የክልሉ ሕዝብ ለበርካታ ዓመታት ሲንከባለሉ የቆዩ፣ ፍትሐዊ እና ሃቀኛ ጥያቄዎች እንዳሉት የክልሉም ሆነ የፌዴራል መንግሥት በውል ያውቃል ነው ያሉት። እነዚህን ጥያቄዎች ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር በመነጋገር በአፋጣኝ ለመፍታት አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ከዚህ በተለየ አካሄድ የሚደረግ የኃይል እንቅስቃሴ የክልሉን ሕዝብ ጥያቄዎች ፍትሐዊነት ጥርጣሬ ውስጥ የሚጥል፣ ሕዝብንም የማያባራ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ ምስቅልቅል ውስጥ የሚከት ነው ብለውታል።
ስለዚህ ሁሉም የክልሉ ሕዝቦች በተለይም ወጣቶች የሰከነ እና ብስለት የተሞላበት አካሄድን በመከተል በአንድነት ለሰላም መቆም አለባቸው ብለዋል። ትርፍ አልባ ከኾነው ከግጭት አዙሪት በዘላቂነት በመላቀቅ ሕዝብን የሚክሱ የመልካም አሥተዳደር እና የልማት ሥራዎች ማከናወን እንደሚገባ በአንክሮ አስገንዝበዋል።
ርእሰ መሥተዳድሩ የአማራ ክልል ሕዝብ ሰላም እና ልማትን አጥብቆ የሚሻ ነው፤ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋርም በጋራ ቁሞ ለሀገር ክብር የሚታትር ነው፣ የዚህን ሕዝብ ሰላም መመለስ ደግሞ የሁላችንም ተቀዳሚ ተግባር ነው ብለዋል።
“የአማራ ክልልን ሕዝብ እወዳለሁ የሚል ሁሉ ለክልሉ ዘላቂ ሰላም ዘብ ይቁም” ሲሉም ተናግረዋል። የክልሉን ሕዝብ ወደ አልባሌ ግጭት ለማስገባት የሚደረግ ማንኛውንም ያልሰከነ አካሄድ የሚከተል አካል ቢኖር እሱ ከክልሉ ሕዝቦች ፍላጎት በተቃራኒ የቆመ ነው ሲሉም ገልጸዋል። ይሕንን ለማስተካከል መንግሥት እና ሕዝብ በፍጹም አንድነት ቁመው መታገል ግድ እንደሚልም ርእሰ መሥተዳድሩ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ:- አሚናዳብ አራጋው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!