
አዲስ አበባ: መስከረም 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) ሰላም ሲኖር የመኖር ተስፋ ይሰነቃል ፤ ስለመለወጥ እና ማደግ ይታቀዳል ፤ ዛሬ ተወድዶ ነገም ይናፍቃል። በተቃራኒው ሰላም ሲናጋና ሲጠፋ ደግሞ ጭንቀት ፣ ተስፋ መቁረጥና ፍርሃት ቦታውን ይይዛል፡፡
ሰላም የምንፈልገውን ያህል እንዳይርቀን ሁሉም ሰው ከራሱ ጀምሮ ሊሠራ እንደሚገባ ነው የወልቂጤ ከተማ ነዋሪዎች ለአሚኮ የተናገሩት።
የሁሉም ነገር ምሰሶና መሠረት ሰላም እንደኾነም አስረድተዋል፡፡ “ሰላምን ከልባችን ከፈለግነው እና ስለሰላም በቅንነት ከሠራን በመዳፋችን ነውም” ብለዋል ነዋሪዎቹ።
የሰላም አስፈላጊነት በውል የሚገባን ባጣነው ጊዜ ነው የሚሉት ነዋሪዎቹ ሰላምን ለማስፈን ከራስ መጀመር እንደሚገባም በአንክሮ ተናግረዋል።
የጦርነትን አውዳሚነት ካለፉት የሀገሪቱ ኹነቶች መረዳት ብልህነት ስለመኾኑም አስገንዝበዋል፡፡ ነዋሪዎቹ “አለመግባባቶችን ሰከን ብሎ ማየትና በዉይይት መፍታት አትራፊ ነው” ብለዋል።
ሰላም በቃላት የሚዘምሩለት ሳይኾን እንዲኖሩት ከሚሹትና ዋጋ ከሚከፍሉለት ቤት ነው ያለው ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- በለጠ ታረቀኝ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!