
ባሕር ዳር: መስከረም 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የ2016 በጀት ዓመት ስምንት የኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመርና ጣቢያዎች ግንባታ ተጠናቅቀው አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ገለጸ።
የተቋሙ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን ተቋሙ ኃይል ማመንጨት፣ የመነጨውን ኃይል ማስተላለፍና በጅምላ የኤሌክትሪክ ሽያጭ ሥራዎችን ያከናውናል።
ኃይልን ተደራሽ ለማድረግ እስካሁን በተከናወኑ ተግባራት ከተለያዩ የኃይል አማራጮች በተገነቡ የኃይል ማመንጫዎች 5 ሺህ 200 ሜጋዋት ኃይል ማመንጨት እንደተቻለ ተናግረዋል።
በ2016ዓ.ም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ተጨማሪ ዩኒቶች ኃይል ማመንጨት ስለሚጀምሩ የሀገሪቱ አጠቃላይ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ይበልጥ እንደሚያድግ ገልጸዋል።
ተቋሙ ከያዛቸው 17 የማስተላለፊያ መስመርና የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶች ውስጥ ስምንቱን በ2016 በጀት ዓመት ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል።
የማስተላለፊያ መስመርና የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶች፤ የደጀን ደብረማርቆስ አሸጎዳ ደሴ ሆርማት፣ ቡታጅራ ወራቤ፣ የአዘዞ ጭልጋ መቱ ማሻ፣ የአዋሽ ወልዲያ ሃራ ገበያ የባቡር መስመር፣ የባሕርዳር ወልዲያ ኮምቦልቻ ፕሮጀክት ውስጥ ከባሕርዳር እስከ ወልዲያ ያለው እንዲሁም የጫካ ፕሮጀክት እንደኾኑም አመላክተዋል።
ከዚህ በተጨማሪ በአዳማ ሁለት እንዲሁም በኮተቤ በሚገኘው የተቋሙ የኃይል ማስተላለፊያ ፕሮጀክት ውስጥ ያሉት ሁለት ፕሮጀክቶች ይገኛሉ ብለዋል።
የበቆጂና ደብረታቦር ማከፋፈያ ጣቢያ፣ የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን እንዲሁም የመቀሌ ዳሎል የማስተላለፊያና ሰብስቴሽን ግንባታ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ለማፋጠን እየተሰራ መኾኑንም ገልጸዋል።
በአራት የአግሮ ፕሮሰሲንግ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የኃይል ማስተላለፊያ መስመር፣ የኢትዮ ጅቡቲ ሁለተኛ ሰርኪዩትና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥልጠናና የልህቀት ማዕከል ግንባታ በተያዘው ዓመት እንደሚጀመሩም ጠቅሰዋል።
ኢዜአ እንደዘገበው ተቋሙ እያከናወናቸው ያሉ ፕሮጀክቶች የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የሚያግዙ መሆናቸውንም ተናግረዋል።
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!