“በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ጉዳት እንዳይደርስ በቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራ ላይ በቅንጅት እየተሠራ ነው” የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን

33

ባሕርዳር፡ መስከረም 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በአየር ንብረት ለውጥ ሊኖር በሚችለው ድርቅና ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ በሚከሰተው ጎርፍ ጉዳት እንዳይደርስ በቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራ ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሠራ መኾኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለፀ።

በኮሚሽኑ የሎጀስቲክስ ኦፕሬሽን ሥራ አመራር ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ደምሴ እንደገለፁት የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎች ሊከሰቱ የሚችሉትን ጉዳቶች ከመቀነስ አንፃር ወሳኝ ሚና አላቸው።

ኮሚሽኑ ከክልሎች፣ ከብሔራዊ ሜትሪዎሎጂ ኢንስቲትዩትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመኾን በቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራዎች ላይ በትብብር እየሠራ መኾኑን ነው ያነሱት።

በተለይም በአየር ኹኔታ መለወጥ ምክንያት ሊኖር የሚችለው ጎርፍና ድርቅ በዜጎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራ ላይ በትኩረት እየተሠራ መኾኑን አመልክተዋል።

አኹን በሀገሪቷ በተለያዩ አካባቢዎች ሊኖር በሚችለው ዝናብ በሚከሰተው ጎርፍም ጉዳት እንዳይደርስ ኅብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግና ከቦታው መነሳትም ካለበት እንዲነሳ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራ እየተሠራ መኾኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ አካባቢ ድርቅ እንዲሁም በደቡብና ደቡብ ምስራቅ የሀገሪቷ አካባቢዎች ደግሞ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ትንበያዎች መኖራቸውንም አክለዋል።

በመሆኑም ከግብርና፣ ጤና፣ የእንስሳት ሀብትና ትምህርት ሴክተሮች ጋር የቅድመ ማስጠንቀቂያ ስራዎችን ተከትለን በቅንጅት መሥራት ይገባናል ሲሉም አስገንዝበዋል ዳይሬክተሩ።

ችግሮቹ ከተከሰቱም የከፋ ጉዳት እንዳያደርሱ መሥራት አለብን ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ለአብነትም ባሮና አዋሽ ወንዞች ሞልተው የተወሰኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተፈናቀሉ ቢኾንም ፈጣን የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርሳቸው መደረጉን አንስተዋል።

ለሚከሰቱት ችግሮች የሚሰጠው የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራን ወስዶ በአግባቡ ካለመተግበር የሚታዩ ችግሮችን እንደ ክፍተት አንስተው፤ በቀጣይ ኅብረተሰቡ ሰፊ ግንዛቤ እንዲያገኝ በየደረጃው ያሉ ባለድርሻ አካላት በትብብር መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተናግረዋል።

ጎርፍና ድርቅ የተከሰተባቸው የሀገሪቷ አካባቢዎች የምግብ እህልና አልሚ ምግቦች በአስቸኳይ ድጋፍ መልክ እንዲደርሱ ኮሚሽኑ ሁለተኛውን ዙር የስርጭት ሥራ እያከናወነ መኾኑንም ኢዜአ ዘግቧል።

በዚህም ከ600ሺህ ኩንታል በላይ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ሩዝ፣ አልሚ ምግብና ከ1 ሚሊዮን ሊትር በላይ የምግብ ዘይት በአሁኑ ወቅት እየተሰራጨ መሆኑን መዘገባችን ይታወሳል።

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous article“በጀቱን በተገቢ ኹኔታ በመጠቀም የሀብት ብክነት እንዳይገጥም መሥራት ይኖርብናል” የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር
Next article“በ2016 ስምንት የኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመርና ጣቢያዎች ግንባታ ይጠናቀቃሉ።”የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል