የአማራ ክልል የገቢዎች ቢሮ ከ1 ሺህ 5 መቶ በላይ ግብር ከፋዮች ላይ እርምጃ ወሰደ፡፡

390

ባሕር ዳር፡- ጥር 22/2012ዓ.ም (አብመድ) የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ የመጠቀም ግዴታ እያለባቸው ያለ ደረሰኝ ክፍያ በፈፀሙ ከ1 ሺህ 5 መቶ በላይ ግብር ከፋዮች ላይ እርምጃ መውሰዱን የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ፡፡

በቢሮው የግብር አወሳሰን፣ አሰባሰብና ክትትል ዳይሬክተር አቶ ይታየው ፈንቴ ጥፋት ለፈጸሙ ግብር ከፋዮች የገንዘብ ቅጣትና የመጨረሻ ደረጃ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ይታየው ገለፃ እርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል 1 መቶ 74 ግብር ከፋዮች ደረሰኝ ሳይሰጡ ክፍያ ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ የተያዙ ናቸው፡፡

እያንዳንዳቸውም የ50 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተወስኖባቸዋል፡፡ ግብር ለመሰወር የሞከሩና የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ ሳይጠቀሙ አገልግሎቱን ሲሰጡ ተደርሶባቸዋል በተባሉ 1 ሺህ 554 ግብር ከፋዮችም የቃልና የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

የገቢ ተቋሙ ከቅጣቱ በፊት ለግብር ከፋዮቹ በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች የሂሳብ መዝገብ የመያዝ ግዴታ እንዳለባቸው፣ በሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን የማከናወንና ደረሰኝ የመስጠት ግዴታ እንዳለባቸው ግንዛቤ ሲፈጥር መቆየቱንም አስረድተዋል፡፡

የግብር ከፋዮችን የሂሳብ መዝገብ አያያዝ ለማሻሻልና ፍትሃዊ ግብር አወሳሰን ስርዓት ለመዘርጋትም ለግብር ከፋዮች ስለሂሳብ መመዝገቢያ ማሽን አጠቃቀም የሚሰጠው ትምህርት ተጠናክሮ የሚቀጥል እንደሚሆንም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በአማራ ክልል 19 ሺህ 685 የደረጃ “ሀ” እና ደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች አሉ፤ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ የመጠቀም ግዴታ ያለባቸው ግብር ከፋዮች ደግሞ 11 ሺህ 509 ናቸው፡፡

ዘጋቢ፡- ኃይሉ ማሞ

No photo description available.
Previous articleየአፍሪካ አየር መንገዶች ወደ ቻይና የሚያደርጉትን በረራ እያቋረጡ ነው፡፡
Next articleየአንበጣ መንጋ በድጋሜ በኢትዮጵያ ተከስቷል፤ ለመከላከሉ ሥራም ጥሪ ቀርቧል፡፡