
ባሕር ዳር: መስከረም 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)የደብረብርሃን ከተማ አሥተዳደር ምክር ቤት 4ኛ ዙር 10ኛ ዓመት 39ኛ አስቸኳይ ጉባኤውን አካሂዷል። በ2016 በጀት ዓመት የገቢ አሰባሰብን በማሳደግና በጀቱን በተገቢ ኹኔታ በመጠቀም የሀብት ብክነት እንዳይገጥም መሥራት እንደሚያስፈልግም ተገልጿል፡፡
የከተማ አሥተዳደሩ ምክር ቤት የኢኮኖሚ በጀትና ፋይናንስ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የኔአንተ አለኽኝ በባለፈው የበጀት ዓመት የተሻለ የገቢ አሰባሰብ የነበረ ቢኾንም ከበጀት አጠቃቀም ጋር ተያይዞ በርካታ ክፍተቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ የሚበጀቱ በጀቶችን ፍትሐዊ ክፍፍል በመሥራት ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራትን መከወን ይገባልም ብለዋል።
ከሁሉም የገቢ አርእስቶች የሚገኙ ሀብቶችን አሟጦ መሰብሰብና መጠቀም እንደሚያስፈልግ ሰብሳቢው ተናግረዋል።
በከተማ አሥተዳደሩ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ለ2016 በጀት ዓመት የመደበኛ ካፒታል በጀት ጸድቋል።
ዘጋቢ፡- ስንታየሁ ኃይሉ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!