
ባሕር ዳር: መስከረም 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በኦልድትራፎርድ አሁንም እየተዘመረለት ነው ፤ ስለ እግር ኳስ ብዙ በማይወራለት ምድር ኾኖም ዓለምን እያስጨበጨ ያለ ኮከብ – ክሪስቲያኖ ሮናልዶ።
አበቃለት ሲባል የጎመራው የኳስ ባለውለታ እግር ኳስን በልፋቱ ነግሶበታል ይሉታል ብዙዎች። ያለመታከት ከዛሬ ነገ የተሻለ ለመኾን ሁሉንም ያደርጋል። ይሄ ታታሪነቱ እድሜው ለአራት አስር ዓመታት ተቃርቦ እንኳ አብሮት አለ።
ባለፈው ዓመት እንደ ንጉሥ ከሚቆጠርበት ማንቼስተር ዩናይትድ በአለመግባባት ወጥቶ ስለ እግርኳስ ብዙ በማይወራበት ሳውዲ ሊግ ሲደርስ ሮናልዶ አብቆቶለታል ተባለ። አዎ ሮናልዶ በእግር ኳስ የፈለገውን አድርጓል ፤ በትልልቅ ክብሮች ደምቋል ፤ አሁን ግን የእግርኳሱ ዓለም የድምቀት ሰው መኾኑን ማመን አለበት ፤ እግር ኳስን ስለ ማቆም ማሰብ እድሜው ያስገድደዋልና።
አብረውት የተጫወቱ እና የእግር ኳሱ ተንታኞች ተመሳሳይ ሃሳባቸውን አንፀባረቁ። ክርስቲያኖ ግን አለ “ዕድሜ ቁጥር ነው ፣ ሰውነቴ የሚነግረኝ ገና መጫዎት እንደምችል ነው። ወደሳውዲ የሄድኩት ለመደበቅ አይደለም ፣ ለሃገሪቱ ሊግ መነቃቃት እና ሌሎች ኮከቦች ሊጉን እንዲቀላቀሉ አረአያ ለመኾን እንጅ።”
የክርስቲያኖ ሃሳብ አሁን ላይ ኾኖ ለመዘነው ሚዛን ይደፋል። አሁን በሳውዲ ምድር እግር ኳስ እንግዳ አይደለም ፤ አሁን የሳውዲ ፕሮ ሊግ የጡረታ መውጫ ማማሟቂያ ሳይኾን የኮከቦች ምርጫ ኾኗል።
በእንግሊዝ ፕሪሜር ሊግ በችሎታቸው አንቱ የተባሉት ሪያል ማህሬዝ ፣ሳድዮ ማኔ ፣ አሌክሳንደር ሚትሮቪች ፣ ንጎሎ ካንቴ ፣ ሮቤርቶ ፌርሚኖን ጨምሮ ብራዚላዊው ኮከብ ነይማር ጁኔር ሳውዲ ገብተዋል። የባሎንዶር አሸናፊው ካሪም ቤንዜማ የሮናልዶን መንገድ ተከትለው ሪያድ ከደረሱት መካከል አንዱ ኾኗል።
እነዚህ ኮከቦች በበዙበት የሳውዲ አረቢያው ቀዳሚ ሊግ ታዲያ ሮናልዶ ቀዳሚ ኾኗል። ባለፈው ዓመት ጥር አልናስርን የተቀላቀለው ክርስቲያኖ ሮናልዶ 16 ጨዋታዎችን አድርጎ 14 ግቦችን አምርቷል። ከወራት በፊት በጀመረው የ2023/2024 የውድድር ዘመን ደግሞ በ8 ጨዋታ 10 ግቦችን ለአል-ናስር አበርክቷል። የሳውዲ ፕሮ ሊግ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪም ነው ሮናልዶ።
ስድስት ኳሶች ደግሞ በፖርቱጋሉ ጥበብ ጣጣቸውን ጨርሰው በቡድን አጋሮቹ መረብ ላይ አርፈዋል። ይህ ቁጥር ሮናልዶን ከኮከብ ግብ አግቢ በተጨማሪ ጎል የኾኑ ኳሶችን በመቻቸትም በሊጉ መሪ እንዲኾን አደርጓታል።
አሁን አብቅቶለታል የተባለው የኳስ ጀግና እንደገና ይሞገሥ ጀምሯል። በወቅቱ የማንቸስተር ዩናይትድ አሠልጣኝ ኤሪክ ቴንሃግ ተገፍቻለሁ ያለው ሮናልዶ አሁን በኦልድትራፎርድ ውጤት ጠፍቶ ጣት ሲቀሰር ደጋፊዎች የድሮ ኮከባቸውን ስም እየጠሩ እየዘመሩ ነው። ሮናልዶ አያስፈልገኝም ያሉት የዩናይትዱ አለቃ ቴንሃግ አሁን የውጤት መንገዱ ጠፍቷቸው ላይ ታች እያሉ ነው።
አስፈሪው የኦልትራፎርድ ግርማ ሞገሥ ተንዶ ክለቡ በቅርቡ በሜዳው ለተከታታይ ሦስተኛ ጊዜ ትንንሽ በሚባሉ ክለቦች ሳይቀር ተሸንፎ የሆላንዳዊውን ወንበር መፋጀት ጀምሯል።በዚያኛው ወገን ደግሞ የሳውዲው አል-ናስር ሮናልዶን ካስፈረመ በኃላ በማሊያ ሽያጭ እና ስፖንሰር ገንዘብ እያፈሰ ነው።
አሁን ላይ በውጤትም አል-ናስር በሳውዲ ፕሮ ሊግ ከመሪው አል-ሂላል በሁለት ነጥብ ብቻ ይበለጣል። ያለፉት ስድስት ተከታታይ ጨዋታዎችንም ሁሉንም አሸንፉል። ሮናልዶም ግብ ማስቆጠሩን ቀጥሎ ከሚታወቅበት የግብ ደስታ አገላለጽ በተጨማሪ በሳውዲዎች ባሕላዊ ጭፈራ ደጋፊዎችን ጮቤ እያስረገጠ ነው።
በአስማማው አማረ
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!