“ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዳይመጡ የሰላሙ ኹኔታ እክል ፈጥሯል” የደቡብ ጎንደር ዞን ትምህርት መምሪያ

33

ባሕር ዳር: መስከረም 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በአማራ ከልል ባሉ ዞኖች ትምርት ለማስጀመር በተደረገው ጥረት በአባዛኞቹ ዞኖች ትምህርት በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ መጀመር ተችሏል፡፡

በክልሉ አብዛኛዎቹ ዞኖች ትምህርት ቢጀመርም ተማሪዎች በሚፈለገው መጠን በትምህርት ገበታቸው እየተገኙ እንዳልኾነ ነው የሚገለጸው፡፡ ለዚህ እንደ ዋና ምክንያት የሚጠቀሰው ደግሞ በየአካባቢው የሰላም ኹኔታው አስጊ በመኾኑ ነው፡፡

በደቡብ ጎንደር ዞን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመጡ እና ትምህርት እንዲጀምሩ ለማድረግ ዝግጅት ተደርጎ ትምህርት ማስጀመር ተችሏል፡፡ ይሁን እንጅ ሁሉም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት እየሄዱ አለመኾኑን የዞኑ ትምህርት መምሪያ ገልጿል፡፡

የደቡብ ጎንደር ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የትምህርት መምሪያ ኀላፊ ደስታ አስራቴ ለአሚኮ እንዳሉት በዞኑ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ 67 በመቶ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው ተመልሰዋል። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ደግሞ 47 በመቶ ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው መገኘታቸውን አስረድተዋል፡፡

ዞኑ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ አስፈላጊውን ሥራ እየሠራ እንደኾነ አቶ ደስታ ነግረውናል፡፡

በተለይም የተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለስ ላይ ትኩረት ተደርጎ እንዲሠራ እና የተማሪ ወላጆች መምህራን ኅብረት ሰፊ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ስለመኾኑም አብራርተዋል፡፡

ኀላፊው የሰላሙ ኹኔታ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዳይመለሱ እያደረገ እንደኾነ ገልጸው ሁሉም ለሰላም ዘብ እንዲቆም አሳስበዋል፡፡

ትምህርት ለአንድ ሀገር እድገት ወሳኝ እንደኾነ በመግለጽም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ሁሉም የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ የመምሪያው ኀላፊ አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ምሥጋናው ብርሃኔ

ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!

Previous articleብልሹ አሠራርን የማይጠየፍ አመራርን እንደማይታገስ የደብረ ብርሃን ከተማ አሥተዳደር አስታወቀ።
Next articleስለ እግር ኳስ ብዙ በማይወራለት ምድር ኾኖም ዓለምን እያስገረመ ያለው ኮከብ።