
ጎንደር: መስከረም 23/2016 ዓ.ም (አሚኮ)በጎንደር ከተማ ከ23ሺህ በላይ ዜጎች የምግብ ዋስትና እና ሴፍቲኔት መርሐ ግብር ተጠቃሚ መኾናቸውን የጎንደር ከተማ ምግብ ዋስትና እና ሴፍቲኔት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።
የጽሕፈት ቤቱ ኀላፊ ሃድያ መሐመድ በጎንደር ከተማ ከ23ሺህ በላይ ዜጎች በመርሐ ግብሩ ተጠቃሚ መኾናቸውን ጠቅሰው ወደ 6ሺህ የሚጠጉት ደግሞ በአካባቢ ልማት እየተሳተፉ መኾናቸውን አብራርተዋል።
በጎንደር ከተማ አንገረብ ቀበሌና አካባቢው በሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች 4 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታና ጥገና መካሔዱን ኀላፊዋ ተናግረዋል።
በሴፍቲኔት የታቀፉ የከተማው ነዋሪዎች በአትክልትና ፍራፍሬም ተሰማርተው እያለሙ መኾኑን ከጽሕፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
“የምግብ ዋስትና እና ሴፍቲኔት መርሐ ግብር ለዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሮ ገቢ ከማስገኘቱ ባሻገር ለከተማው ልማትም አዎንታዊ ድርሻ እየተወጣ ነው” ብለዋል ኀላፊዋ፡፡
የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎችም በመንገድ ጥገና እና ግንባታ እንዲሁም በፅዳትና አረንጓዴ ውበት ሥራዎች እየተሳተፉ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ዘጋቢ፡- አገኘሁ አበባው
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!